ባለስልጣኑ እንስሳትና የእንስሳት ተዋፅኦ ምርቶችን ጥራትና ደህንነት ለማረጋገጥ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር እየሰራ መሆኑን ገለጸ

66

አዳማ፤ ሚያዝያ 09/2016 (ኢዜአ)፦እንስሳትና የእንስሳት ተዋፅኦ ምርቶችን ጥራትና ደህንነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ብቁ ሙያተኞችን ለማፍራት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር እየሰራ መሆኑ የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ገለፀ።

በባለስልጣኑ የእንስሳት ምርት ጥራት ቁጥጥር መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አያሌው ሹመት ለኢዜአ እንደገለጹት እንስሳትና የእንስሳት ተዋፅኦ ምርቶች ጥራትና ደህንነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ናቸው።

በእንስሳትና የእንስሳት ተዋፅኦ ምርቶች ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የጥራት መጓደልና ሌሎች ችግሮችን ቀድሞ መለየት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ስራዎች ተጀምረዋል ብለዋል።

ይህም በቄራዎችም ሆነ በሌሎች በእንሰሳት ተዋጽኦ ምርቶች አምራች ተቋማት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያላቸውን ችግሮች ቀድመው ለመለየት ጭምር የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ ስጋና የስጋ ምርቶች ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃን ያሟሉ መሆናቸውን የሚያረጋግጡ ብቁ ሙያተኞችን ለማፍራት ከአጫጭር ስልጠናዎች ጀምሮ የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አስረድተዋል።

በዚህም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ጤና ኮሌጅ ጋር በመተባበር ተከታታይ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች እየተሰጡ እንደሆነ አክለዋል።

የአቅም ግንባታ ስልጠናው የስጋ ምርቶች ተቀባይ ሀገራት መስፈርትና ፍላጎትን ያሟሉ የእንስሳት ተዋጽኦ ምርት ለማቅረብ ብቁ የሰው ሃይል ለመፍጠር ያለመም ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንድማገኝ አሰፋ በበኩላቸው በዘርፉ ዓለም አቀፍ የጥራት አጠባበቅና አስተዳደር መስፈርት ማስጠበቅ እንዲሁም ሙያተኞች ያላቸው ክህሎት፣ ብቃትና እውቀት ደረጃ በተከታታይ ማሳደግ እንደሚገባ መክረዋል።

በተጨማሪም በእንስሳት፣ በስጋና የስጋ ተረፈ ምርቶች ምርመራ ቤተ ሙከራዎች ጥራትና የደህንነት ደረጃ አጠባበቅም ከዚሁ ጋር አብሮ መጠናከር እንዳለበትም ጠቁመዋል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም