የ2016 ኢትዮጵያ  ታምርት የጎዳና ላይ ሩጫ  ሊካሄድ ነው -ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር  

124

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2016(ኢዜአ)፡- የ2016 ኢትዮጵያ  ታምርት 10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በመጪው ሚያዚያ 13 በአዲስ አበባ  እንደሚካሄድ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር  አስታወቀ። 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ  ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ፤ በ2016 ኢትዮጵያ ታምርት  የጎዳና ላይ ሩጫ ከ10ሺህ በላይ ሰዎች እንደሚሳተፉ ገልፀዋል።

በተጨማሪም ከ22 ክለቦች  የተውጣጡ አትሌቶች እንዲሁም  ዲፕሎማቶች እንደሚሳተፉም አብራርተዋል። 

ሩጫው የኢንዱስትሪ ምርቶች ለአገር ኢኮኖሚ  ያላቸውን አስተዋጽኦ ለማስተዋወቅና ምርታቸውን እንዲያሳድጉ ለማድረግ፣ በአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች የሚመረቱ የስፖርት ትጥቆችን ለአለም ለማስተዋወቅና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ያለመ እንደሆነ ተናግረዋል።

በኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚሰሩ ባለሙያዎች የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት እንደሆነም ገልፀዋል።

በሩጫ ውድድሩ አሸናፊ ለሚሆኑት ከ50 ሺህ እስከ 250ሺህ ብር ሽልማት እንደተዘጋጀም ጠቁመዋል።

የሩጫው መነሻና መድረሻ መስቀል አደባባይ እንደሆነም ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም