የሸዋል ኢድ በዓልን አብሮነትን በሚያጎለብት መልኩ እያከበርን ነው - የበዓሉ ተሳታፊዎች

88

ሐረር ፤ ሚያዚያ 9/2016(ኢዜአ)፡- የሸዋል ኢድ በዓል አብሮነትና ወንድማማችነትን በሚያጎለብት መልኩ እያከበሩ መሆናቸውን የበዓሉ ተሳታፊዎች ተናገሩ።

የ"ሸዋል ኢድ" በዓል የክልሉ ነዋሪዎች፣ ከአጎራባች ክልል፣ ከተለያየ የሀገሪቱ ክፍል እና ከውጭ ሀገራት የመጡ እንግዶች በተገኙበት ከትናንት ጀምሮ  በድምቀት እያከበሩት ይገኛሉ።

የሰላምና የፍቅር በዓል የሆነውን ሸዋል ኢድ በአጎራባች ክልል የባህል ቡድኖች  በልዩልዩ አልባሳትና ጭፈራዎች ደምቆ እየተከበረ መሆኑን ነው አስተያየታቸውን ለኢዜአ  የሰጡ ታዳሚዎች የገለጹት።

በስነ-ሥርዓቱ ላይ የቀረቡት የተለያዩ ባህላዊ ትርኢቶችም በዓሉን ይበልጥ እንዳደመቀው ታዳሚዎቹ ገልጸዋል።


 

የዘንድሮው ሸዋል ኢድ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስ  እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም በማይዳሰስ ቅርስነት በተመዘገበበት ወቅት የሚከበር በመሆኑ ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ  በድምቀት እየተከበረ እንደሚገኝ ነው የገለጹት።

ከታዳሚዎቹ መካከል ወጣት ሀናን ዮኒስ እንደምትገልጸው የሸዋል-ኢድ በዓል የኢድ አልፈጥር በዓል ከተከበረበት ቀን ጀምሮ ለተከታታይ ስድስት ቀናት ከተፆመ በኋላ ከስድተኛው ቀን ምሽት ጀምሮ እስከ ማግስቱ 10 ሰዓት ድረስ የሚከበር ነው ብላለች።

በበዓሉ በተለይ ወጣቶች የሚተጫጩበት መሆኑን የጠቆመችው ወጣት ሃናን፤ ዘንድሮም ከሌሎች አካባቢና ከውጭ ከመጡ እንግዶች ጋር በአብሮነት  በድምቀት  እያከበሩት እንደሆነ ተናግራለች።

የሸዋል ኢድ በዓል ዘንድሮ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም በማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገቡና "የዓለም ሀብት በመሆኑ በዓሉን ለየት አድርጎታል" ያለው ደግሞ ወጣት ዚያድ አርጋው ነው።

በዓሉን ከሁሉም ወንድምና እህቶቻቸው ጋር   በጋራ እንያከበሩት መሆኑን የጠቀሰው ወጣት ዚያድ፤  እንዲህ ዓይነት የፍቅርና የአብሮነት ምንጭ የሆኑ ባህሎችን ለትውልድ ማስቀጠል እንደሚገባ አመልክቷል።

ወይዘሮ ኢሊሊ አሊ በበኩላቸው ሸዋል ኢድ በዓል በሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ታጅቦ  በዓሉን በአብሮነት እና በደማቅ ሁኔታ በማክበር  የኔነት ስሜትን መፍጠሩን ተናግረዋል።

በተለይም በዓሉ በዓለም በማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገቡ እጅግ እንዳስደሰታቸው የተናገሩት ወይዘሮ ኢሊሊ፤ በዓሉ እሴቱ ሳይሸራረፍ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ የበኩላቸውን እንደሚያበረክቱ ተናግረዋል።

ከሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የመጡት የበዓሉ ታዳሚ አቶ አብዶ ሂሎሀሰን  በበኩላቸው፤ በበዓሉ   ባዩት ዝግጅት  መደሰታቸውንና ከተለያየ እምነት ተከታዮችና ብሄረሰቦች ጋር በጋራ ማክበራቸው ልዩ ስሜት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል፡፡ 

መሰል በዓላት የህዝቦች ትስስርና የአብሮነት እሴትን የሚያጎለብቱ በመሆናቸው መጠናከር ይገባቸዋል ሲሉም ተናግረዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም