ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ለሚሰራቸው ስራዎች ውጤታማነት የበኩላችንን እንወጣለን- የባሌ ዞን የህብረተሰብ ተወካዮች

258

ሀዋሳ ፤ ሚያዚያ 9/2016(ኢዜአ)፡- ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ለሃገር ሰላም፣ አንድነትና ልማት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ በመረዳት ለውጤታማነቱ የበኩላችንን እንወጣለን ሲሉ በኦሮሚያ ክልል የባሌ ዞን የተለያዩ የህብረተሰብ ተወካዮች ገለጹ።

ኮሚሽኑ በበኩሉ በክልል ደረጃ የሚደረገውን የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ በቅርቡ ለመጀመር ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጿል።

በአጀንዳ ልየታ የሚሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎችን የመምረጥ ሂደት በተከናወነበት ወቅትም የምክክር ኮሚሽኑ እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራት ስኬታማ እንዲሆኑ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ የባሌ ዞን የተወካዮች ምርጫ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

ከባሌ ዞን ሮቤ ከተማ የመጡት ወይዘሮ ፋጡማ ሃጂአልዬ ''የሃገር ሰላም በተለይ ሴቶችን ተጠቃሚ ስለሚያደርግ በሰላም አምባሳደርነት መስራት አለብን" ብለዋል።

ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽን አለመግባባትንና ግጭትን በውይይት በመፍታት ለሃገር ሰላም የሚያበረክተው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ ከተወካይ መረጣ ጀምሮ በንቃት በመሳተፍ ሃላፊነታቸውን እየተወጡ እንደሆነ ተናግረዋል።

"የምክክር ሂደቱ ሁሉንም አሳታፊ ማድረጉ ለስኬታማነቱ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸው ህዝቡ ከእኔነት ይልቅ እኛ የሚለውን የጋራ አስተሳሰብ እንዲያጎለብት እየሰራሁ ነው" ብለዋል።

ሌላው አስተያየት ሰጪ በዕድሮች ተወክለው በመድረኩ የተሳተፉት አቶ ተስፋዬ ቂሊጦ በበኩላቸው በሃገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የህዝቡ ተስፋ ትልቅ መሆኑን ገልጸዋል።

"ሂደቱም ሁሉን አሳታፊ በመሆኑ ችግሮቻችንን ለመፍታት የሚወከሉ አካላትን ተመካክረን እንድንመርጥ የተሰጠንን እድል በተገቢው በመጠቀም እንደ ዜጋ ሃላፊነታችንን መወጣት አለብን" ብለዋል።

የምክክር ኮሚሽኑ በሃገር ሰላም አንድነትና ልማት ላይ በጋራ እንድንሰራ ያመቻቸውን መድረክ ወደ ዕድል ቀይሮ ሃገራዊ ሃላፊነትን መወጣት እንደሚገባ ያነሱት ደግሞ አባገዳ መለሰ ረታ ናቸው።

በባህል የተሰጣቸው የአባገዳነት ማእረግ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው በመሆኑ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በሽምግልና የመፍታት እድል እንደሰጣቸው ተናግረዋል።

እንደሃገር የሚፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶችን በውይይት የመፍታት የቆየ ልምዳቸውን በማካፈል የዜግነት ግዴታቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር አምባዬ ኦጋቶ በበኩላቸው በክልሉ የሚደረገውን የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ በቅርቡ ለመጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

ከክልል አጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረኮች ሶስት ዋና ዋና ተግባራት የሚጠበቁ ሲሆን ከየአካባቢው የሚመጡ የህብረተሰብ ተወካዮች በሚያቀርቧቸው አጀንዳዎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር መወያየት ቀዳሚው ነው።

የሃገራዊ ምክክር ተግባር ሂደት ነው ያሉት ዶክተር አምባዬ ሂደቱ አሳታፊ፣ አካታች፣ ግልጽና መተማመን ያለበት እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።


 

ከተወካዮች የፊት ለፊት አጀንዳ ማሰባሰብ በተጨማሪ ኮሚሽኑ ባዘጋጀው የተለያየ አጀንዳ የማሰባሰብ ዘዴ በርካታ ሃሳቦችን እየተቀበለ መሆኑን ደግሞ የገለጹት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ ናቸው።

ኮሚሽኑ የአጀንዳ መቀበያ ሳጥኖችን፣ ድረ ገጾችን፣ ፖስታ፣ ኢሜይልና ሌሎች የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም አጀንዳ እየተቀበለ መሆኑን ገልጸዋል።

ሃገራዊ ምክክር በህዝብ የሚመራ ፕሮጀክት በመሆኑ ህዝቡ በተለያዩ አማራጮች ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል ሻሸመኔ ክላስተር ከባሌ ዞን 11 ወረዳዎች ከተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ በአጀንዳ ልየታው የሚሳተፉ 176 ተወካዮችን ማስመረጡን መዘገባችን ይታወሳል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም