በክልሉ በዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ ኢኒሼቲቭ ከለማው መሬት ከ68 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተሰብስቧል

65

ሮቤ ፤ሚያዚያ 9/2016(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮው የበጋ መስኖ የስንዴ ልማት ኢኒሼቲቭ ከለማው መሬት ከ68 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል የሚበልጥ ምርት መሰብሰቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ። 

የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹና ሌሎች የክልሉ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በባሌ ዞን የከርሰ ምድር ውኃን በመጠቀም የበጋ ስንዴን በመስኖ እያለሙ የሚገኙ የአጋርፋ ወረዳ አርሶ አደሮችን ማሳ ጎብኝተዋል። 

አቶ ጌቱ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፣ የክልሉ መንግስት አርሶ አደሩ የተለያዩ የውኃ አማራጮችን በመጠቀም እንዲያለማ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። 

በክልሉ በተለይም አርሶ አደሩ የምግብ ዋስትናውን ከማረጋገጥ በተጓዳኝ ገበያን ማዕከል አድርጎ እንዲያለማ በተሰጠው ትኩረት ከሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር በላይ በበጋ መስኖ ስንዴ ማልማት ተችሏል። 

በእስከ አሁኑ ሂደትም ከአንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የነበረ ሰብል በማሰባሰብ ከ68 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ማግኘት መቻሉን አቶ ጌቱ አመልክተዋል። 

የተቀረው ልማትም እንደየአካባቢው የሥነ ምህዳር ሁኔታ በመሰብሰብ በዘንድሮ የበጋ መስኖ ልማት ኢኒሼቲቭ ለመሰብሰብ የታቀደውን 105 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማሳካት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። 

በልማቱ ከተሳተፉ የአጋርፋ ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል አቶ ሁሴን አህመድ በሰጡት አስተያየት፣ ከዚህ በፊት የዝናብ ውኃን ብቻ ጠብቀው በሚያካሄዱት የግብርና ሥራ ከውኃ እጥረት የተነሳ የልፋታቸውን ያህል ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ሲያደርጋቸው እንደነበር ነው ያስታወሱት፡፡ 

ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ከዝናብ ውኃ በተጨማሪ በአካባቢያቸው የሚገኙ የውኃ አማራጮችን በመጠቀም በሚያለሙት የስንዴ ልማት ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡  

በበጋ ወቅት መስኖን በመጠቀም ስንዴን ማልማት መቻላቸውን አርሶ አደር ስዩም ጎሳ ተናግረው ከአንድ ሄክታር የስንዴ ማሳ እስከ 45 ኩንታል መሰብሰባቸውን ገልፀዋል፡፡

መንግስት ከሌሎች የአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር በረዥም ጊዜ ብድር ያመቻቸላቸው የውኃ መሳቢያ ሞተር ልማቱን አስፍተው እንድሄዱ መነሳሳትን እንደፈጠረላቸው በማከል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም