በአማራ ክልል ከ224 ሺህ በላይ ተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር ተጠቃሚ ሆነዋል

81

ባህር ዳር ፤ ሚያዚያ 9/2016(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ከ224 ሺህ በላይ ተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር  ተጠቃሚ መሆናቸውን  የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ኢየሩስ መንግስቱ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ በመሆን ላይ የሚገኙት  በ454 ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ናቸው።


 

ከክልሉ መንግስት፣ ከመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ከህብረተሰቡ የተገኘ 151 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦ መረሃ ግብሩ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

መርሃ ግብሩ ትምህርት የሚያቋርጡ  ተማሪዎች ቁጥር በመቀነስ  ትምህርታቸውን ተረጋግተው በመከታታል  ለትምህርት ጥራትና ተደራሽነት መረጋገጥ አስተዋጽኦ እንዳለው አስታውቀዋል።

በክልሉ መረሃ ግብሩ እየተተገበረ ካለባቸው መካከል በደብረ ብርሃን ከተማ የአንድነት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ባዩ ኃይለጊዮርጊስ በበኩላቸው እንዳሉት፤ በመርሃ ግብሩ 1ሺህ 968 ተማሪዎች ተጠቃሚ በመሆን ላይ ናቸው።

ተማሪዎችን ቁርስና ምሳ በመመገብ የጥናትና የክፍል ውስጥ ተሳትፏቸው እንዲጨምር ከማስቻሉም በላይ ትምህርታቸውን ይደግሙና ያቋርጡ የነበሩ ተማሪዎች ችግር ለማቃለል እንዳስቻለ ገልጸዋል።


 

ምገባ ከተጀመረ ወዲህ ትምህርቱን ትኩረት ሰጥቶ በመከታተል የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ መጀመሩን የገለጸው ደግሞ የትምህርት ቤቱ የ8ኛ ክፍል ተማሪ ያፌት አዲስ ነው።

የዚሁ ትምህርት ቤት ተማሪ ቤዛዊት አበጋዝ በበኩሏ ፤በትምህርት ቤቱ በሚካሄደው የምገባ መርሃ ግብር የትምህርት ተሳትፎዋን ከማሳደጉም በላይ ውጤቷ እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግራለች። 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም