"አስተውሎት" የተሰኘው ሳይንሳዊ ፊልም ታዳጊዎች ለዘመኑ የሳይንስ ጥበብ ያላቸውን መሻት የሚጨምር ነው - ተማሪዎች

196

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2016(ኢዜአ)፡- "አስተውሎት" የተሰኘው ሳይንሳዊ ፊልም ታዳጊዎች ለዘመኑ የሳይንስ ጥበብ ያላቸውን መሻት የሚጨምርና የኢትዮጵያን ተስፋ የሚያሳይ መሆኑን በፊልሙ ምርቃት ላይ የታደሙ ታዳጊ ተማሪዎች ተናገሩ።

በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የተዘጋጀ ''አስተውሎት'' የተሰኘ ሳይንሳዊ ፊልም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት ተመርቋል።

በዕውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ በተዘጋጀው በዚህ ፊልም ላይ አንጋፋ እና አዳዲስ ተዋንያን የተሳተፉበት ሲሆን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ የደረሰበትን ደረጃ፣ የኢትዮጵያን ተሞክሮና የመጪውን ትውልድ ተስፋ የሚያስቃኝ ነው።

በፊልሙ ምረቃ ላይ የተገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች፤ ፊልሙ በተለይም የሳይንስ ጥበብ ዝንባሌ ያላቸውን ታዳጊዎች ህልም የሚያሳካ መሆኑን ገልጸዋል።

የጥቁር አንበሳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ቃልአብ ሲሳይ እና ብሌን ኤልያስ ፊልሙ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሳይንሳዊ ጥበብ ያለውን ሁለንተናዊ ፋይዳ በቅጡ የተገነዘብንበት ነው ብለዋል።

በሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ የሚሰሩ የኪነ ጥበብ ስራዎች ታዳጊዎች ከተለምዷዊ ሙያ በተጨማሪ የተግባር እውቀት ያገኙበት መሆኑንም ተናግረዋል።

የገላን የወንዶች አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆኑት አብዲ መገርሳ፣ ኤባ ዓለሙና በረከት ደስታ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሰራቻቸውን አበረታች ስራዎች ከፊልሙ መገንዘባቸውን ገልጸዋል።

ታዳጊዎች ወደ ፊት በሳይንስ መስክ ልቀው ለመውጣትና ሀገራቸውን ለማገልገል ትልቅ ፍላጎት እንዲያድርባቸው የሚያደርግ የጥበብ ስራ መሆኑን አንስተዋል።

አዲሱ ትውልድ በዲጂታሉ ዓለም በእውቀትና በፈጠራ ብቁና ተፎካካሪ እንዲሆን ዘመኑን የሚመጥን የትምህርት መሰረተ ልማት እና ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ወላጆችና ተቋማት ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም