በክልሉ አርሶ አደሩ ምርቱን ለገበያ አቅርቦ ተጠቃሚ እንዲሆን ለመሰረተ ልማት ግንባታ ትኩረት ተሰጥቷል

274

ሚዛን አማን ፤ ሚያዚያ 8/2016(ኢዜአ)፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል አርሶ አደሩ ምርቱን በቀላሉ ለገበያ አቅርቦ ተጠቃሚ እንዲሆን ለመሠረተ ልማት ግንባታ ትኩረት መሰጠቱ ተገለጸ።

በደቡብ ቤንች ወረዳ በ18 ሚሊዮን ብር ለሚገነባው የዛን ወንዝ ድልድይ የመሠረተ ድንጋይ ተቀምጧል።

የመሰረት ድንጋዩን ያስቀመጡት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በወቅቱ እንደገለጹት፣ አርሶ አደሩ ከሚያመርታቸው የግብርና ምርቶቹ የተሻለ ተጠቃሚ መሆን እንዲችል የመንገድና የድልድይ መሠረተ ልማቶች ትልቅ ሚና አላቸው።

በመሆኑም አርሶ አደሩ ምርቱን ገበያ እውጥቶ የሚገባውን ጥቅም እንዲያገኝ የክልሉ መንግስት ለድልድይና ለመንገድ መሰረተ ልማቶች ልዩ ትኩረት ሰጥቷል ብለዋል።

በዛሬው ዕለትም በደቡብ ቤንች ወረዳ በ18 ሚሊዮን ብር ለሚገነባው የዛን ወንዝ ድልድይ የመሰረተ ድንጋይ መቀመጡን ገልጸው፣ በሌሎችም አካባቢዎች መሰል የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

የደቡብ ቤንች ወረዳ በልማትና የግብርና ኤክስቴንሽን ስርፀትን ተግባራዊ በማድረግ በክልሉ ካሉ ወረዳዎች ግንባር ቀደም ወረዳ መሆኑንም አመልክተዋል።

ወረዳው ከ500 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ በኩታ ገጠም የለማ ሙዝ ያለው ብቸኛ ወረዳ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህን የልማት አቅም ለማሳደግ ለመሠረተ ልማት ግንባታ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።

ድልድዩ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ህዝብን ከህዝብ እንዲሁም ምርትና ገበያን እንደሚያገናኝ ተናግረዋል።


 

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወልዱ በጪ በበኩላቸው እንደገለጹት በአካባቢው ከፍተኛ የቡና፣ የበቆሎ፣ የሙዝ እና የቅመማ ቅመም ምርቶች ቢኖሩም የመሠረተ ልማት ችግር ያለበት ነው።

የአካባቢው አርሶ አደሮች የግብርና ምርት በጀርባቸው ተሸክመው ለገበያ እንደሚያወጡ ጠቁመው፤ ወረዳው ባለፉት ሁለት ዓመታት ችግሩን ለመቅረፍ በህብረተሰቡ ተሳትፎ ሦስት ድልድዮችን ገንብቶ ለአገልግሎት ማብቃቱን ተናግረዋል።

በቀጣይም የሕዝቡን ድጋፍ በማጠናከር የመንገድ መሠረተ ልማት ጥያቄን ለመመለስ በትኩረት እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል። 


 

የድልድዩን የግንባታ ሥራ የሚያከናውነው "ተስፋዬ አሰፋ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ" ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ አሰፋ በበኩላቸው ግንባታውን በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ለማስረከብ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል የጃንቹታ ቀበሌ አርሶ አደር አዳሙ አኩሙ "መንግስት የመንገድ ችግራቸውን ለመፍታት የጀመራቸው የልማት ሥራዎች በእርሻ ሥራችን የተሻለ ተጠቃሚ እንድንሆን የሚያስችል ነው" ብለዋል።

እስከዛሬ ያመረቱትን የበቆሎ፣ የቡናና የሙዝ ምርት በሸክምና በፈረስ ጭኖ ለገበያ የሚያቀርቡበትን አድካሚ ሁኔታ እንደሚያስቀርላቸው የተናገሩት ደግሞ በአካባቢው የኮብ ቀበሌ አርሶ አደር አብዮት ካሽት ናቸው።

በመንገድና ድልድይ እጦት ምክንያት ምርቶቻቸውን ሽጠው ለመጠቀም ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰው ድልድይ ሲጠናቀቅ ችግራቸውን እንደሚቃለል ተናግረዋል።

በመሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ መርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ የተለያዩ የሥራ ሃላፊዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም