በአገር አቀፍ ደረጃ  ገበያውን ለማረጋጋት ዘርፈ ብዙ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ

147

ሆሳዕና ፤ ሚያዝያ 8/2016 (ኢዜአ)፡- በሀገር አቀፍ ደረጃ  ገበያንና የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ዘርፈ ብዙ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረ መስቀል ጫላ ገለጹ ።

በሚኒስትሩ የተመራ ቡድን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወራቤና ቡታጅራ ከተሞች የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎችን በመስክ ተመልክቷል።

በዚህ ወቅት ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ስልቶችን በመከተል ገበያንና  የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት  ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በተለይም ገበያውን ለማረጋጋት የምርት መጠን ማሳደግ ላይ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

ለዚህም በየአካባቢው አርሶ አደሩ በሌማት ትሩፋትና በከተማ ግብርና እንዲሁም ያለውን አማራጭ ተጠቅሞ እያደረገ ያለውን ጥረት ጠቅሰዋል።

እንዲሁም የሸማችና ህብረት ስራ ማህበራትንና ዩኒየኖችን  በማጠናከርና በመደገፍ  ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በአምራች ኢንዱስትሪው፣ በህብረት ስራ ማህበራትና በዩኒየኖች እየተከናወነ የሚገኘው ተግባር የሚበረታታ ነው ብለዋል።

በዚህም ምክንያት አልባ በሆነ የዋጋ ጭማሪና ህዝብን ለምሬት የሚዳርጉ አካላትን ለመቆጣጠር የሚያስችል አሰራር መኖሩን በመስክ ምልከታው ማረጋገጥ መቻላቸውን ገልጸዋል።


 

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ይስሐቅ ማሶሬ፤  በክልሉ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት አደረጃጀትና የቁጥጥር ስርዓትን የማጠናከር ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል

በዚህም አርሶ አደሩ፣አምራች ኢንደስትሪውና የሸማቾች ህብረት ማህበራት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲጫወቱ የሚያስችል  አደረጃጀት መፍጠር መቻሉን አስረድተዋል።

በክልሉ "ከሳምንት እስከ ሳምንት"  በሚል ተነሳሽነት ሸማቹንና አምራቹን በቀጥታ የሚያገናኘው ገበያ ያለማቋረጥ እንዲቀጥልና ምርት በሚደብቁት ላይ በሚደረግ ቁጥጥር ውጤት መምጣቱን ጠቅሰዋል።

በክልሉ ገበያን ለማረጋጋት የሚያግዙ አማራጮችን ማህበረሰብ ባሳተፈ መልኩ እየተከናወነ ውጤት እየተገኘበት መሆኑን ተናግረዋል።

ቡታጅራ ከተማ የ"አገልግል ሸቀጣሸቀጦች ማከፋፈያ" ህብረት ስራ ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ዮሐንስ ገላን በበኩላቸው፤ ማህበሩ ባለፈው ዓመት  መጨረሻ አካባቢ 200 አባላት ይዞ ወደስራ መግባቱን ገልጸዋል።

 በወቅቱ አስተዳደሩ ባደረገው ድጋፍና በአባላቱ አስተዋጽኦ በ2 ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል ስራ የጀመረው ማህበሩ ነዋሪውን መጥቀም ብቻ ተጠቃሚ በመሆኑ ገቢው መጨመሩን ተናግረዋል።

"ከሳምንት እስከ ሳምንት ገበያ“ ሳምንቱን ሙሉ የግብይት ስርዓት ተግባራዊ መደረጉ አስፈላጊውን ግብዓት ተመቻችቶላቸው እንዲሸምቱ ማስቻሉን  የተናገሩት ደግሞ በወራቤ ከተማ 01 ቀበሌ ነዋሪ  ወይዘሮ ሂክማ ነስረዲን ናቸው።

በሚኒስትሩ የተመራው ቡድን በሁለቱም ከተሞች በዩኒየኖችና በሌሎች አደረጃጀቶች ገበያንና የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን ተዘዋውሮ ተመልክቷል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም