የኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭትን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት በተቀናጀ መልኩ መጠናከር አለበት - ጤና ሚኒስቴር

232

ሀዋሳ ፤ሚያዚያ 8/2016 (ኢዜአ)፦የኤች አይ  ቪ/ኤድስ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረጉ ጥረቶች በተቀናጀ መልኩ ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

ሀገር አቀፍ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ፕሮግራም የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም የጋራ ግምገማ መድረክ በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

በግምገማው ላይ የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍቃዱ ያደታ እንደገለጹት የኤች አይቪ /ኤድስ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረጉ ጥረቶች ሊጠናከሩ ይገባል።

ከዚህ ቀደም የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችና አካባቢዎች ላይ በማተኮር ከግንዛቤ ማስጨበጫ ጀምሮ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት መገኘቱን አስታውሰዋል።

“በፈቃደኝነት ምርመራ የማድረግ ልምድ ማደግና አጋላጭ ምክንያቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ የስርጭት ምጣኔውን በሀገር ደረጃ ከአንድ በመቶ በታች ማድረስ እንደተቻለ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በተፈጠረ መዘናጋት የበሽታው የስርጭት መጠን ከፍ እያለ መምጣቱን ጠቅሰው፣ የህብረተሰቡን መዘናጋት በማስወገድ ስርጭቱን ለመግታት በትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

አቶ ፍቃዱ እንዳሉት ቀደም ሲል በተሰሩ ሥራዎች የተገኘው ስኬት በሁሉም ባለድርሻ አካላት ላይ መዘናጋት እንዲፈጠር አድርጓል።

ይህም በአሁኑ ወቅት ለሚታየው የበሽታው ስርጭት መጠን መጨመር ምክንያት መሆኑን ጠቅሰው፣ መዘናጋቱን አስወግዶ ስርጭቱን ለመቆጣጠር አቅምን በማስተባበር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።  

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ፕሮግራም መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር ዶክተር ተስፋዬ ዘርፉ እንዳሉት፣ በክልሉ ከፍተኛ የሰዎች እንቅስቃሴ ያለባቸውን አካባቢዎች በመለየት የበሽታውን ስርጭት የመቆጣጠር ሥራ እየተሰራ ነው።


 

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችና የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት ተደርጎ በተሰራው ሥራ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች በፈቃደኝነት የኤች.አይ.ቪ ምርመራ ማድረጋቸውንና 5 ሺህ የሚሆኑት ቫይረሱ በደማቸው እንደተገኘባቸው ገልጸዋል።

ቫይረሱ የተገኘባቸው ወደሕክምና ክትትል ገብተው መድሀኒት እንዲጀምሩ ለማድረግ በተሰራው የማማከር ሥራም 95 በመቶ የሚሆኑት መድሀኒት ጀምረዋል ብለዋል።

የጋምቤላ ክልል ጤና ቢሮ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ አስመላሽ አበራ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በክልሉ በተለይ ከፍተኛ የወርቅ ማዕድን የሚገኝባቸውና የኢንቨስትመንት አካባቢዎች ላይ በሽታውን ለመከላከል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።


 

በክልሉ ከባህል ጋር ተያይዞ የወንዶች ግርዛት በማይፈጸምባቸው አካባቢዎች ያለውን የኤች አይ ቪ ተጋላጭነት ለመቀነስም የግንዛቤ ማጎልበቻ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በክልሉ የቫይረሱ ስርጭት 3 ነጥብ 6 በመቶ መሆኑን የጠቀሱት አስተባባሪው፣ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ከጤና ሚኒስቴር እና ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአራት ቀናት በሚካሄደው የግምገማ መድረክ የሁሉም ክልሎች የኤች.አይ.ቪ ዘርፍ ሀላፊዎችና አጋር ድርጅቶች የተገኙ ሲሆን የክልሎች አፈጻጸም ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት ታውቋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም