የክልሉን መንግስት ጥሪ በመቀበል ዘጠኝ የጽንፈኛ ቡድን ታጣቂዎች እጃቸውን በሰላም ሰጡ - ኮማንድ ፖስቱ

412

ጎንደር ፤ ሚያዚያ 8/2016(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን የክልሉ መንግስት ያደረገውን ጥሪ በመቀበል  ዘጠኝ የጽንፈኛ ቡድን ታጣቂዎች ከነትጥቃቸው እጃቸውን በሰላማዊ መንገድ መስጠታቸውን የዞኑ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ምክትል ሃላፊና የኮማንድ ፖስቱ አባል አቶ አንተነህ ታደሰ አስታወቁ።

ለጽንፈኛው ቡድን ታጣቂዎች በሰላም እጅ ሰጥቶ መመለስ የዞኑ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ተጠቁሟል።

እጃቸውን ለመንግስት የሰጡት የጽንፈኛ ቡድን ታጣቂዎች በበኩላቸው፤ በተሳሳተ መንገድ ተወናብደን የገባንበት ዓላማ ለእኛም ሆነ ለአማራ ህዝብ የሚጠቅም አይደለም ብለዋል፡፡ 


 

የመምሪያው ምክትል ሃላፊና የዞኑ ኮማንድ ፖስት አባል አቶ አንተነህ ታደሰ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ የቡድኑ ታጣቂዎች በተሳሳተ መንገድ በመንቀሳቀስ ህዝባቸውን ሲጎዱ መቆየታቸውን ጠቁመው፤  በድርጊታቸው በመጸጸት የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው መግባታቸውን አስታውቀዋል፡፡ 

በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን በመስጠት ወደ ሰላማዊ ኑሮ እንዲመለሱ በማድረግ ረገድ የዞኑ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸውም ገልጸዋል፡፡

የጽንፈኛ ቡድን ታጣቂዎች ካለፈው ስህተታቸው በመማርና በመጸጸት ወደ ህብረተሰቡ ተቀላቅለው የበደሉትን ህዝብ በሚክሱ የሰላምና የልማት ተግባራት እንዲሰማሩ ይደረጋል ብለዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ያስተላለፈውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ቀደም ሲል ወደ ዞኑ የገቡ 1ሺ 700 የሚሆኑት የተሃድሶ ስልጠና ተሰጥቷቸው ወደ ህብረተሰቡ በመቀላቀል ሰላማዊ ህይወት እየመሩ እንደሚገኙም አስረድተዋል፡፡

ህዝባችንን ከማጎሳቆልና ከወንድሞቻችን ጋር ደም ከመቃባት ውጪ ያተረፍነው ምንም ነገር የለም ያለው  የሻለቃ መሪ እንደሆነ የገለጸው አቶ ሙሉቀን ምስጋናው ነው፡፡

በተሳሳተ መንገድ ወደ ጫካ ብገባም  ሰላምን ከማሳጣትና ልማቱን ከማደናቀፍ ውጪ መፍትሄ እንደማይገኝ በመገንዘቤ  የሰላም አማራጭን ለመከተል ወስኛለሁ ብሏል፡፡

እጁን ለመንግስት የሰጠው ሌላው የጽንፈኛው ቡድን ታጣቂ አቶ አየልኝ ማሞ በበኩሉ፤ በተሳሳተ መንገድ የገባንበት ችግር  የእርስ በርስ መጠፋፋት ካልሆነ በስተቀር የህዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ እንደማያስችል ተናግሯል፡፡

ዓላማ የለሽና የህዝብን እልቂት በሚያባብስ ተግባር የተሰማሩ ወገኖቻችን አሁንም የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደ ሰላማዊ ህይወት እንዲገቡ ጥሪ እናቀርባለን ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም