በጋምቤላ ክልል ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የህብረተሰቡ ሚና ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል

265

ጋምቤላ ፤ ሚያዝያ 8/2016 (ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል ዘላቂ ሰላም ለማስፈን መንግስት ከሚያከናውናቸው ተግባራት በተጨማሪ የህብረተሰቡ ሚና ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለፁ። 

በክልሉ በኑዌር ዞን ከሚገኙ አምስት ወረዳዎች የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በወቅታዊ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ዛሬ በኝንኛንግ ከተማ መክረዋል። 

ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይት መድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ ክልሉ አለመግባባቶችን በውይይት ፈትቶ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በመንግስት በኩል ትኩረት ተሰጥቷል። 

በክልሉ ህዝቦች መካከል ያለው የወንድማማችነትና እህትማማችነት እሴት ይበልጥ ሊናጠናክር ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ከመንግስት ጥረት ጎን ለጎን የህብረተሰቡ ሚናም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል። 


 

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ቴንኩዌይ ጆክ በበኩላቸው፤ በክልሉ ለአካባቢው ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የሚተርፍ የተፈጥሮ ሃብት መኖሩን አስታውሰዋል። 

በመሆኑም የመሬትና የተፈጥሮ ፀጋዎች ለአካባቢው የፀጥታ ችግሮች መንስኤ ሳይሆን፤ ለብልጽግናችን ልናውል ይገባል ብለዋል። 

አብሮነታችንና አንድነታችንን በመጠበቅ ሰላማችንና የጋራ ተጠቃሚነታችን ለማረጋገጥ ጠንክረን ልንሰራ ይገባል ሲሉም ገልጸዋል። 



ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ዶፕ ሙን በሰጡት አስተያየት፤ በክልሉ የፀጥታ ችግሮች ሲከሰቱ በጋራ ተወያይቶ የመፍታት ባህላችንን የበለጠ ልናጠናክር ይገባል ነው ያሉት። 

ወይዘሮ ኛሾም ቾን በበኩላቸው፤ በክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት እውን እንዲሆን መንግስት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ ተናግረዋል። 

በክልሉ ለህግ የበላይነት መስፈን ህዝቡም አመራሩም ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት የተናገሩት ሌላው የመድረኩ ተሳታፊ አቶ ራች ሬስ ናቸው። 

በውይይት መድረኩ ላይ የክልል፣ የዞንና የወረዳ የአመራር አባላትን ጨምሮ ተዋቂ ግለሰቦች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ወጣቶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም