ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሀይል ትስስር በመፍጠር ቀጣናዊ የመሪነት ሚና እየተጫወተች ነው- ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)

523

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 8/2016(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሀይል ትስስር በመፍጠር ቀጣናዊ የመሪነት ሚና እየተጫወተች መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

'world Future Energy Summit' የፓን አፍሪካዊ ትብብር ሚና የታዳሽ ሀይል ልማት ከማሳለጥና የኢነርጂ ዋስትና የማረጋገጥ አላማውን አድርጎ በአቡዳቢ ከአፕሪል 16 እስከ 18/2024 የምክክር መድረክ በመካሄድ ላይ ነው።

በመድረኩ ላይ ገለጻ ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ቀጣናዊ የሀይል ትስስር መሰረት የመጣልና የማጠናከር ጉዳዮች ኢትዮጵያ በቀጣናው ለትብብርና ቅንጅት ትኩረት መስጠቷን ገልጸዋል።

በዚህም ሱዳናውያን የገጠማቸው ውስጣዊ ችግር ክፍያ እንዲፈጽሙ ባያስችላቸውም የሀይል አቅርቦት መቀጠሉን እንደማሳያ አንስተዋል፡፡

ሚኒስትሩ አክለውም ኢትዮጵያ ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን የምስራቅ አፍሪካ ፓወር ፑልን ለማጠናከርና ለማስቀጠል አይነተኛ ሚና እየተጫወተች መሆኗን ጠቁመዋል።

በዚህም የሀይል መስመሮች፣ መንገዶችና የቴሌኮም ኔትወርኮችን ጨምሮ ሌሎች መሰረተ ልማቶች ወደ ጎረቤት ሀገራት ተዘርግተው እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ብሔራዊ እቅድ ቀጣናዊ ቅንጅታዊ ስትራቴጂ መካተቱንና በአህጉር ደረጃ ለማሳደግ ታሳቢ መደረጉን ማንሳታቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

እንደሀገር ያለን የሀይድሮፓወር እምቅ አቅምን የማልማት ልምድ መኖሩንና ተቋም መገንባት መቻሉ የምስራቅ አፍሪካ የአረንጓዴ ኢነርጂ ማዕከል ለመሆን እንድንሰራ አስችሎናል ብለዋል፡፡

የመንግስትና የግሉ ዘርፍ አጋርነትን በመተግበር የግሉን ዘፍፍ በሀይል ልማት ዘርፍ ለማሳተፍ ያለው ቁርጠኝነት አንዱ ማሳያ መሆኑንም ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አህጉራዊ የሀይል ሲስተም ማስተር ፕላን መሰረት በማድረግ ለሶስት ጎረቤት ሀገራት የሀይል ትስስር መፈጠሩንና ሌሎች ሀገራትን በማካተት ትስስሩን ይበልጥ ለማጎልበት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የሀይል መሠረተ ልማት ግንባታና ዝርጋታ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ የሚጠይቅ በመሆኑ የልማት አጋሮች ቁርጠኝነት እጅግ አስፈፈላጊ መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በሀይል ልማት ኢንቨስትመንት መሰማራት በቀጣናው የስራ ዕድል ፈጣራ እና የሰላምና የጸጥታ ጉዳዮች ላይ አስተዋጽኦ ማድረግ ነው ሲሉም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም