በሲዳማ ክልል ከ28 ሚሊዮን በላይ የተሻሻሉ የቡና ችግኞች ለተከላ ተዘጋጁ

260

ሀዋሳ፤ ሚያዚያ 8/ 2016 (ኢዜአ) ፡-  በሲዳማ ክልል የቡናን ልማትን ለማስፋፋት ከ28 ሚሊዮን በላይ የተሻሻሉ የቡና ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውን  የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በተጨማሪም  2 ነጥብ 9 ሚሊዮን የአቦካዶ ችግኞችም መሰናዳታቸውም ቢሮው ገልጿል።


 

የክልሉ የ2016 በጀት ዓመት የቡናና ፍራፍሬ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዛሬው   በሸበዲኖ ወረዳ  በይፋ በተጀመረበት ውቅት የቢሮው ሃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ በወቅቱ እንደተናገሩት፤  በክልሉ የቡና ምርታማነትን በጥራት ለማሳደግ ለተሻሻሉ  የቡና ዝርያ ትኩረት ተሰጥቷል።

በክልል እስካሁን 165 ሺህ ሄክታር መሬት በቡና ተክል መሸፈኑን አውስተው፤ ልማቱን ለማስፋፋት ዘንድሮ 10 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የቡና ችግኞች እንደሚተከሉ  አስረድተዋል።

ለዚህም ከ28 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኞች መዘጋጀታቸውን አሰታውቀዋል።

ከተከላው ጎን ለጎንም ያረጁ ቡናዎች ነቀላና ጉንደላም በትኩረት ይከናወናል ብለዋል።

በተጨማሪም እየተካሄደ ያለውን ልማት ለማስፋፋት ዘንድሮ 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን የአቦካዶ ችግኞች መሰናዳታቸውን ገልጸዋል።

 በዚህም 4 ሺህ 500 ሄክታር አዲስ መሬት እንደሚለማ ጠቅሰው፤ የፍራፍሬ  ችግኝ ተከላውም ከአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ጋር ተቀናጅቶ የሚካሄድ መሆኑን አስረድተዋል።

የሲዳማ ክልል ቡና ፣ ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን  ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ቃሬ በበኩላቸው፤ በክልሉ በሄክታር የሚገኘውን 9 ነጥብ 5 ኩንታል የቡና ምርት ወደ 11 ነጥብ 5 ለማሳደግ መታቀዱን ገልጸዋል።


 

ለዚህም የቡና ምርትና ምርታማነት የሚጨምረው ፓኬጅ ሙሉ በሙሉ ለመተግባር አርሶ አደሩን ባለሙያውና አመራሩን ግንዛቤ በማሳደግ የቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የቡናን ምርታማነት ለመጨመር የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ተፈጥሯዊ ቡና ለአለም ገበያ ለማቅረብና የአርሶ አደሩን ገቢ ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰዋል።

ለዚህም  3 ነጥብ 2 ቶን የተፈጥሮ ማዳበሪያ  መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።

ክልል አቀፍ የቡናና ፍራፍሬ ችግኝ ተከላ የተጀመረበት የሸበዲኖ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኤሊያስ አየለ፤  በወረዳው ከ10 ሺህ 250 ሄክታር በላይ መሬት በቡና ልማት የተሸፈነ እንዳለ ተናግረዋል።


 

ዘንድሮ  የቡና ሽፋኑን ለማሳደግ በ527 ሄክታር አዲስ የቡና ተከላ እንደሚከንና  ከ1 ሚሊዮን በላይ የተሻሻለ ዝርያ የቡና ችግኞች መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።

በሸበዲኖ ወረዳ የፉራ ቀበሌው አርሶአደር ካሳ ተኮን በሰጡት አስተያየት፤ ዘንድሮ 1ሺ 500 የተሻሻሉ የየቡና ችግኞችን እንደሚተክሉ ገልጸዋል።  


 

በማሳቸው በተካሄደ የተከላ መርሃ ግብርም በርካታ ችግኞች መተከላቸውን ጠቅሰው፤ ከዛሬ ጀምሮ እስኪ ሚያዚያ አጋማሽ ባለው የተከላው ተግባር  እንደሚያጠናቅቁ ተናግረዋል።

ክልል አቀፉ የቡናና ፍራፍሬ ችግኝ ተከላ በሸዲኖ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች መጀመሩንና በዚህም  የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም