ለሀገር ዘላቂ ሰላምና አብሮነት ያለ ምንም ልዩነት ሁሉም በጋራ ሊቆም ይገባል - የሃይማኖት መሪዎች

258

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 8/2016(ኢዜአ)፡- ለሀገር ዘላቂ ሰላምና አብሮነት ያለ ምንም ልዩነት ሁሉም በጋራ ሊቆም ይገባል ሲሉ   የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ገለጹ።

የሰላም ጉዳይ የሀገር ህልውና መሠረትና የዜጎችም ሁለንተናዊ ዋስትና በመሆኑ የጋራ ጥረትና ትብብር የሚጠይቅ መሆኑ ይታወቃል።

በሰላምና ልማት እንዲሁም በመልካም ስነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ በመገንባት ረገድ በተለይም ደግሞ የሃይማኖት ተቋማት ድርብ ኃላፊነት እንዳለባቸው ይነሳል።  

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ ሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ከምንም በላይ የሰላም ጉዳይ የሁላችንም የጋራ አጀንዳ መሆን አለበት ብለዋል።

ከግጭት አዙሪት በመውጣት ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የዜጎች ሁሉ ትብብር ሊታከልበት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት  ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፤ የሰላም ጉዳይ የሁሉም ነገር መሠረት በመሆኑ ለሰላማችን በጋራ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

የሰላም መጓደል ሲያጋጥም የበርካታ ውስብስብ ችግሮች ምክንያት መሆኑን የተለያዩ አገራትን ነባራዊ ሁኔታ ማየት በቂ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም በጋራ መቆም ይጠበቅብናል ሲሉ ተናግረዋል።

በተለይም የሃይማኖት ተቋማት የሰላምን ጉዳይ የመደበኛ ሥራቸው አካልና የዘወትር ተግባራቸው አድርገው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡

በእስልምና እምነት የአብሮነት፣ የሰላምና የሰብዓዊነት ጉዳይ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን ጠቅሰው፤ ይኸው ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።


 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ሊቀ-አይላፍ ቀሲስ እያሱ ናሁሰናይ፤ በሀገር ሰላም ጉዳይ በጋራ ለመሥራት የሁሉም ጥረትና ዝግጁነት ግድ መሆኑን ገልፀዋል።

በተለይ አሁን ላይ እንደ ሀገር እየገጠሙን ላሉ ችገሮች ዘላቂ መፍትሔ ለመሻት በሚደረገው ጥረት ቤተክርስቲያኗ የሚጠበቅባትን ሚና ለማበርከት ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።


 

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ፤ በምድር ሁሉ ሰላም እንዲሰፍን መፀለይና ማስተማር የጋራ እሴቶቻችን ናቸው ብለዋል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚከሰቱ ችግሮችን በንግግር መፍታት ሁነኛ አማራጭ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ የሃይማኖት ተቋማት ሚናቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ለሀገር ሰላም ለሚደረጉ ሁለንተናዊ ጥረቶች የድርሻዋን የምትወጣ መሆኑንም አረጋግጠዋል።


 

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ-ክርስቲያናት ሕብረት ፕሬዝዳንት ፓስተር ፃዲቁ አብዶ በበኩላቸው፤ የሃይማኖት ተቋማት በሰላምና ልማት ዙሪያ አብሮነትና የጋራ ጥረታቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን ገልፀዋል። 

በግጭትና ጦርነት ሞትና ኪሳራ እንጂ አንዳችም የሚገኝ ውጤትና መፍትሔ አለመኖሩን ጠቅሰው፤ ሁላችንም የሰላም እጆቻችንን ልንዘረጋ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም