የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭት የሀገርን ሰላም እየፈተነ በመሆኑ ለዘላቂ መፍትሄ በጋራ መስራት ይገባል

423

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 8/2016(ኢዜአ)፡- የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭት የሀገርን ሰላም እየፈተነ በመሆኑ ለዘላቂ መፍትሄ በጋራ መስራት እንደሚገባ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ገለጸ። 

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት ያለበትን ሁኔታ የተመለከተ የዳሰሳ ጥናት ሪፖርት ይፋ አድርጓል።


 

የሪፖርቱ የመጀመሪያ መረጃዎች ከፌስቡክ፣ ቲክቶክ፣ ቴሌግራም፣ ዩ-ቲዩብና ኤክስ በናሙና የተሰበሰቡ ናቸው።

ሁለተኛው ደግሞ በክልሎች በመጠይቆችና በነፃ የስልክ መስመር የሕዝብ አስተያየት የተሰበሰቡ መሆኑ ተገልጿል።

የባለሥልጣኑ የመገናኛ ብዙኃን አቅም ግንባታ ዴስክ ኃላፊ ኤደን አማረ በሰጡት ማብራሪያ፤ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ እየተስፋፋ መሆኑን ከተሰበሰበው መረጃ መረዳት ችለናል ብለዋል። 

በተለይም ብሔርን ሃይማኖትን እና ፖለቲካዊ አመለካከትን መሰረት በማድረግ ህዝብን በጠላትነት የሚፈርጁ እና አንዱ ለሌላው ስጋት የሚያስመስሉ የሃሰት መረጃዎች በስፋት መሰራጨታቸውን ጠቁመዋል።

እንደ አጠቃላይ የጥላቻ ንግግር አስጊነት ካለፈው አመት አንጻር በይዘትም በአቀራረብም ተባብሶ የቀጠለ መሆኑን ተናግረዋል።

በጥቂት ደቂቃዎች በርካታ መረጃዎች የሚጋሩበት መድረክ እንደመሆኑ መጠን ይህንን የሚመጥን በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር መዘርጋት እንደሚገባም ተናግረዋል።

የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ማስፈጸሚያ ደንብ ሊወጣለት እንደሚገባም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዮናታን ተስፋዬ፤ የሪፖርቱ ዓላማ የማኅበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ግዴታቸውን በምን ያህል መጠን እየተወጡ ነው የሚለውን ለማመላከትመሆኑን ገልጸዋል።


 

የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭት የሀገርን ሰላም እየፈተነ በመሆኑ ለዘላቂ መፈትሄ ለማሻትም የሪፖርቱን አስፈላጊነት አንስተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም በኢትዮጵያ ለሚከሰቱ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የጥላቻ ንግግሮች እና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ትልቁን ድርሻ የሚይዝ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በማህበራዊ ሚድያ የሚሰራጩ የጥላቻና ሀሰተኛ ንግግሮችን በህግ ለመከላከልና ለመቆጣጠር አዋጅ ቁጥር 1185/12 የተደነገገ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም