የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 108 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ

229

አዲስ አበባ ፤ሚያዝያ 8/2016 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 108 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አደም ኑሪ ለኢዜአ እንዳሉት ቢሮው በ2016 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት 109 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ 108 ቢሊዮን ብር የሰበሰበ ሲሆን አፈጻጸሙም 98 ነጥብ 5 በመቶ ነው።

ገቢው ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ45 በመቶ እድገት ወይም የ34 ቢሊዮን ብር ጭማሪ ማሳየቱን ጠቅሰዋል።

በ2015 በጀት ዓመት በአጠቃላይ ከተሰበሰበው 107 ቢሊዮን ብር ገቢ ጋር ሲነጻጸር ደግሞ የ1 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው።

ቢሮው ገቢውን የሰበሰበው ከቀጥታ ታክስ፣ ቀጥተኛ ካልሆኑ ታክስ አገልግሎቶች ፣ ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ እና ሌሎችም መሆኑን አስረድተዋል።

ሕገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል፣ የታክስ አከፋፈል አገልግሎት ለማሻሻል በዲጂታል የታገዙ አሰራሮች እየተተገበሩ መሆኑንም የቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል።

ቢሮው በሀሰተኛ ደረሰኝ የሚፈፀም ግብይትን ለመቆጣጠር ባደረገው ክትትል ከ5 ሺህ በላይ ግብይቶች በሀሰተኛ ደረሰኝ መፈጸማቸውን ማረጋገጡን ገልጸዋል።

በሀሰተኛ ደረሰኝ ግብይት ሲፈፅሙ የተገኙ ግብር ከፋዮች ላይም 225 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ቅጣት በማስከፈል አስተዳደራዊ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ጠቁመዋል።

አቶ አደም በበጀት ዓመቱ ከ140 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፥ ለዚህም ስኬት ሁሉም በየደረጃው ርብርብ እንዲያደርግና ግብር ከፋዩም በታማኝነት ግብሩን እንዲከፍል አሳስበዋል።

የምንከፈለው ግብር ለራሳችን ጥቅም መሆኑን መገንዘብ ይገባል ያሉት ኃላፊው፤አዲስ አበባ የምታመነጨውን ያህል ገቢ ለመሰብሰብ የግብር ከፋዩ፣ የአመራሩና የማህበረሰቡ ቅንጅታዊ አሰራር ወሳኝ መሆኑንም እንዲሁ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም