በዩኒቨርሲቲው እየተገነባ ያለው የባዮ ጋዝ ማብላያ ፕሮጀክት የተቋሙን የሃይል ችግር ከመፍታት ባለፈ የግብርና ሥራን ያሳልጣል 

323

ሶዶ ፤ሚያዝያ 8/2016 (ኢዜአ)፦ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ እየተገነባ ያለው የባዮ ጋዝ ማብላያ ፕሮጀክት የተቋሙን የሃይል ችግር ከመፍታት ባለፈ፤ ለአካባቢው ግብርና ልማት መሳለጥ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

ፕሮጀክቱ በአገሪቱ በዓይነቱ የመጀመሪያውና በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚከናወን ሲሆን፣ ከሁለት ወራት በኋላ ለአገልግሎት እንደሚበቃም ተገልጿል።

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ የሚመራ የፌዴራልና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች  ቡድን ዛሬ ፕሮጀክቱን ጎብኝቷል።

ሚኒስትር ደኤታው ዶክተር ኢንጂነር ሱልጣን በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፣ በዩኒቨርሲቲው እየተገነባ ያለው ባለ 300 ሜትር ኪዩብ የባዮ ጋዝ ማብላያ ፕሮጀክት በዓይነቱ የመጀመሪያ ነው።


 

የፕሮጀክቱ ግንባታ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የሚፈጅ ሲሆን፣ ግንባታው ሲጠናቀቅ 25 ኪሎ ዋት ሃይል ማመንጨት እንደሚችልም አስታውቀዋል።

ከባዮ ጋዙ  የሚመነጨው ሃይል የተቋሙን የሃይል ችግር  ከማቃለል ባለፈ፤ ከባዮ ጋዝ  የሚገኘው ተረፈ ምርት የግብርና ልማት ሥራዎችን ለማከናወን እንደሚያስችል አስረድተዋል።

በተጨማሪም የአካባቢው አርሶ አደሮች የባዮ ጋዙን ተረፈ ምርቱን በመጠቀም ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ያስችላቸዋል ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ በኢትዮጵያ እስካሁን በግለሰብ ደረጃ በተገነቡ አማራጭ የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሆኑ 46 ሺህ አባወራዎች ናቸው።


 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ምክትልና የማዕድንና ኢነርጂ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ኦላዶ ኦሎ በበኩላቸው በክልሉ በቤተሰብ ደረጃ የተገነቡ ባዮ ጋዝ ፕሮጀክቶች በርካታ አባወራዎችን ተጠቃሚ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

አሁን ላይ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ እየተገነባ ያለው ፕሮጀክት በዓይነቱ ከፍተኛ የሆነና በተቋም ደረጃ እየተካሄደ ያለ ፕሮጀክት መሆኑን አመልከተዋል።

ይህም የክልሉን ሃይል የማመንጨት አቅም ከማሳደግ ባለፈ የአካባቢውን አርሶ አደሮች በግብርና ልማት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አቶ ኦላዶ ተናግረዋል።


 

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በግብርናና በማዕድን ሀብት ልማት የልህቀት ማዕከል ለመሆን አቅዶ እየሠራ ነው ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ አሸናፊ አበበ ናቸው።

ፕሮጀክቱ ዩኒቨርሲቲው እያከናወነ ያለውን የግብርና ሥራን ከማገዝ ባለፈ የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን ለማከናወን ፋይዳው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ከሁለት ወራት በኋላ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃም አቶ አሸናፊ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ከአምስት ሚሊዮን በላይ አባወራዎችን ከባዮ ጋዝ በሚመነጭ ሃይል ተጠቃሚ የሚያደርግ አቅም እንዳላት ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያሳያል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም