የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ከ23ኛ ሳምንት ጀምሮ በሃዋሳ ይካሄዳሉ

613

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 8/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ከ23ኛ ሳምንት ጀምሮ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም እንደሚካሄድ የፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ደግሞ ሚያዚያ 19 እና 20 ቀን 2016 ዓ.ም ይደረጋሉ።

የፕሪሚየር ሊጉ መርሐ ግብር ከ16ኛ ሳምንት አንስቶ በድሬዳዋ ስታዲየም እየተከናወነ ሲሆን፥ የ22ኛ ሳምንት ጨዋታዎችም ከሚያዚያ 10 እስከ 13 ቀን 2016 ዓ.ም በድሬዳዋ ይካሄዳሉ።

የሊጉ መርሐ ግብር በኢትዮጵያ ዋንጫ ምክንያት ከተቋረጠ በኋላ ወደ ውድድር ሲመለስ የ23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ከሚያዚያ 24 እስከ 27 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚካሄዱ የሊጉ አክሲዮን ማህበር አመልክቷል።

እስከ 27ኛ ሳምንት ያሉ ጨዋታዎች በሃዋሳ እንደሚደረጉም ተገልጿል። 

ከ28ኛ እስከ 30ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚከናወን ማህበሩ ከዚህ ቀደም መግለጹ ይታወቃል።

የሊጉ ውድድር ሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር መርሐ ግብር በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም መካሄዱ የሚታወስ ነው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም