ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጋር በመተባበር ለወጣት ሴቶች የሙያ ስልጠና መስጠት ጀመረ

101

ድሬዳዋ ፤ሚያዚያ 8/2016(ኢዜአ)፡- ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጋር በመተባበር በምስራቅ ሐረርጌ ወረዳዎች ስራ ለሌላቸው ወጣት ሴቶች የሙያ ስልጠና መስጠት ጀመረ።

ስልጠናው በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ላይ ለሶስት ወራት ሲሆን ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ የተደረጉት 50  ሴቶች መሆናቸው ታውቋል።

በስልጠናው ማስጀመሪያ መርሃግብር ላይ የተሳተፉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዑባህ አደም(ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ የሚገኙ የስራ አጥ ወጣቶችን ጥያቄዎች ለመመለስ የተቀናጀ ጥረትና ርብርብ ያስፈልጋል።

መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው የተጀመሩ ጥረቶችና ተስፋዎች የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጡ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።

በዚህ ረገድ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመቀናጀት እየሰጠ ያለው ስልጠና ወጣቶቹ ሙያዊ ዕውቀትና ክህሎት ታጥቀው የስራ ባለቤት እንዲሆኑ የሚያግዛቸው ነው ብለዋል።

ዩኒቨርስቲው ባለው ሃብት፣ ዕውቀትና ልምድ በመታገዝ የስራ ዕድል ለመፍጠርና ለማስፋት የሚከናወኑ ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ የሚያደርገውን እንቅስቃሴዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

"በዚህ ዘርፍ ከዩኒቨርሲቲው ጋር መስራት ለሚፈልጉ አካላት በራችን ክፍት ነው" ብለዋል ዶክተር ዑባህ።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የማህበራዊና የልማት ኮሚሽን የሐረር ቅርንጫፍ ምክትል ፕሮግራም ኃላፊ አቶ ግርማ ከበደ በበኩላቸው ፕሮግራሙ የሴቶችንና የወጣቶችን ማህበራዊና የስራ ችግሮች ለማቃለል ያለመ ስራ ይሰራል ብለዋል።

ዛሬ ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የተዘጋጀው የሙያና የክህሎት ስልጠና ለዚህ አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከስልጠናው በኋላ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረግላቸዋል ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም