የዕድሮችና የዕድር ምክር ቤቶች የምዝገባና የዕውቅና አሰጣጥ መመሪያ ወደ ሥራ ገባ 

185

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 8/2016(ኢዜአ)፡-  የዕድሮችና የዕድር ምክር ቤቶች የምዝገባና የዕውቅና አሰጣጥ መመሪያ 151/2016 ተግባራዊ መሆን መጀመሩን የአዲስ አበባ ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ።

የአዲስ አበባ ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ መመሪያውን በተመለከተ ከአዲስ አበባ ዕድሮች ምክር ቤቶች ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።

በቅርቡ ወደ ሥራ የገባው ይህ መመሪያ የተዘጋጀው ዕድሮች ሕጋዊ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ ታሪካዊና የመደጋገፍ ባህላዊ እሴታቸውን ጠብቀው ለትውልድ እንዲሸጋገሩ የሚመዘገቡበትና ዕውቅና የሚያገኙበት ሥርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ መሆኑን ተጠቅሷል።

ዕድሮች ከቀብር ማስፈጸም ባሻገር በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ አባሎቻቸውንና የከተማውን ነዋሪ ጠቃሚ እንዲሆኑ ከሚመለከተው አካል ድጋፍ የሚያገኙበት ሥርዓት ለመዘርጋት መሆኑን በመመሪያው ተመላክቷል።

በመመሪያው መሠረት በአዲስ አባበ የሚገኙ ሁሉም እድሮችና የእድር ምክር ቤቶች ምዝገባ እንደሚያካሂዱና በየዓመቱ እድሳት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተመላክቷል።   

ይህንንም ተከትሎ የዘንድሮ ምዝገባ ከመጪው ሓምሌ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ይጀምራል ተብሏል።    

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ገነት ቅጣው በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ዕድሮች አሰራራቸውን በማዘመን ኢትዮጵያዊ እሴቶችን ጠብቀው የአሰራር ሥርዓትን በማበጀት በማኅበራዊና ኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲያሳድጉ ዕድል የሚሰጥ ነው። 

ዕድሮች የኅብረተሰቡን አብሮ የመኖር፣ የመተሳሰብና የመደጋገፍ እሴት በነፃነት ለማራመድ በዘመናዊ መልክ እንዲደራጁ መመሪያው ይጋብዛል ብለዋል። 

ይህም እድሮች ኢትዮጵያዊ እሴቱን ጠብቆ በዘመናዊ መልክ ተደራጅተው ለትውልድ እንዲተላለፉ  እንደሚያስችል አስረድተዋል።

ዕድሮችና የዕድር ምክር ቤቶች የአሰራር ሥርዓታቸውን በማዘመን ከአዲስ አበባ ሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ጋር በዳታቤዝ ለማስተሳሰር እንደሚሰራም ተናግረዋል።


 

የአዲስ አበባ ዕድሮች ጥምረት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ታምራት ገብረ ማርያም በበኩላቸው ዕድሮች ከቀብር ማስፈጸም ባሻገር ወደ ልማት በመግባት አሰራራቸውን ከማዘመን ባለፈ አቅማቸውንም የሚያጎለብት መመሪያ መሆኑን ገልጸዋል።

የዕድሮችና የዕድር ምክር ቤቶች የምዝገባና የዕውቅና አሰጣጥ መመሪያ ለሌሎች ክልሎችም አርአያ የሚሆንና ዕድሮችን ለማገዝ ድጋፍ የሚሰጥ ነው ብለዋል።

የአሰራር መመሪያው ቀጣይ ሥራቸውን ለማጠናከር ሕጋዊ አቅም በመሆን ከመንግሥት የቴክኒክና የሙያ ድጋፍ ለማግኘት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ከ7 ሺህ 500 በላይ ዕድሮች እንዳሉ ፕሬዝዳንቱ አቶ ታምራት ገልጸዋል።  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም