የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ የህክምና ባለሙያዎች ለሴቶች ጤና ድጋፍ የሚያደርግ በጎ አድራጎት ማህበር አቋቋሙ 

247

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 8/2016(ኢዜአ)፦የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ የህክምና ባለሙያዎች "ሔዋን" የተሰኘና ለሴቶች ጤና ድጋፍ የሚያደርግ በጎ አድራጎት ማህበር ማቋቋማቸውን ይፋ አደረጉ፡፡

በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ የማህጸንና ጽንሰ ስፔሻሊስት ሃኪምና የማህበሩ የቦርድ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ድልአየሁ በቀለ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት በሆስፒታሉ ወሊድን ጨምሮ የማህጸንና የጡት ካንሰር፣ የኩላሊት ህክምናና ሌሎች ውስብስብ የጤና አገልግሎቶች ይሰጣሉ።

ህክምናውን ፈልገው ከሚመጡ ተገልጋዮች መካከል እናቶች፣ሴቶችና ህጻናት ትልቁን ቁጥር እንደሚይዙ ጠቁመው፤አብዛኞቹ የመረጃና የፋይናንስ እጥረት እንዳለባቸው አብራርተዋል።

በተለይ ለህክምና የሚያስፈልጋቸውን ወጪ ለመሸፈን የገንዘብ እጥረት እንደሚያጋጥማቸውና የተገልጋዮች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ነው ያነሱት፡፡

ይህም ካጋጠማቸው የጤና እክል ባልተናነሰ መልኩ ኢኮኖሚያዊ ጫና እየፈጠረባቸው እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ አኳያ በሆስፒታሉ በጎ ፍቃደኛ የህክምና ባለሙያዎች ተነሳሽነት ''ሔዋን'' የተሰኘ ለሴቶች ጤና ድጋፍ የሚያደርግ በጎ አድራጎት ማህበር ተመስርቷል ብለዋል።


 

በሆስፒታሉ የማህጸንና ጽንስ ስፔሻሊስት እና የማህበሩ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ወንድሙ ጉዱ በበኩላቸው ማህበሩ የህክምና እርዳታ የሚያገኙ እናቶች ያሉባቸውን የግንዛቤ ክፍተት መሙላት ላይ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ለሚያጋጥማቸው የፋይናንስ እጥረት የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ህክምናቸው እንዳይስተጓጎል ማድደረግም ዋነኛው ተግባር መሆኑን አስረድተዋል።

አንዳንድ የህክምና ሂደቶች ረዥም ጊዜን የሚወስዱ በመሆናቸው ታካሚዎቹ በተረጋጋ ሁኔታ ህክምናቸውን እንዲከታተሉ ጊዜያዊ ማረፊያ የማቋቋም እቅድ መያዙንም ጠቁመዋል።

መንግስት የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋት ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በጤና ሚኒስቴር የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ስራ አስፈጻሚ ፋጡማ ሰኢድ ናቸው።


 

በተለይም የእናቶችና ህጻናት ሞት ቅነሳ ላይ ትኩረት በማድረግ በተሰሩ ስራዎች አበረታች ውጤት ቢመዘገብም አሁንም ይበልጥ መስራት እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡

በመሆኑም በዘርፉ የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡


 

የሔዋን የሴቶች የጤና ድጋፍ በጎ አድራጎት ማህበር በጎ ፍቃደኛ አምባሳደር አርቲስት የትናየት ታምራት፤  ሁሉም ለድርጅቱ የአቅሙን እገዛ በማድረግ ለእናቶችንና ህጻናትን ሞት ቅነሳ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ጥሪ አቅርባለች፡፡

 

 

 

 

 

 

 

   

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም