ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ይፋ ያደረገው ተናባቢ "ኪው አር ኮድ" ምንድን ነው? ምን ዓይነት ጥቅምስ ይኖረዋል? 

218

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 8/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያለጥሬ ገንዘብ ፈጣንና ቀልጣፋ የክፍያ ሥርዓት መፈጸም የሚያስችል ተናባቢ "ኪው አር ኮድ" አገልግሎት ይፋ አድርጓል። 

መንግሥት የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓቱን ለማዘመንና ዜጎች ሁሉን አቀፍ የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ ነው። 

በዚህም አሁን ላይ በኢትዮጵያ ዲጂታል የክፍያ ሥርዓት ምኅዳር እየሰፋ መሆኑን ነው በብሔራዊ ባንክ የክፍያ ሒሳብ ማወራረጃ ሥርዓት ዳይሬክተር ሰለሞን ዳምጠው የሚናገሩት።  

ይህንንም ተከትሎ ዜጎች ፈጣንና ቀልጣፋ የክፍያ አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ በባንክ ሒሳባቸው አማካኝነት የዲጂታል ክፍያ ሥርዓትን መጠቀም የሚያስችላቸውን መሠረተ-ልማት እየተሟላ መሆኑን ገልፀዋል።

ከእነዚህም መሠረተ-ልማቶች መካከል በ"ኪው አር ኮድ" አማካኝነት የሚፈጸሙ ክፍያዎች አንደኛው  መሆኑን ጠቅሰዋል። 

በዚህም አንድ ግለሰብ ደንበኛ ከሆነበት ባንክ ወይም ከሚጠቀመው የሞባይል ዋሌት ባገኘው "ኪው አር ኮድ" ጋር ተዛማጅ በሆነ ሥርዓት በማናበብ ክፍያ መፈጸም ይችላል። 

አሁን ላይ ደግሞ ከዚህ ቀደም በተዘበራረቀ "ኪው አር ኮድ" አማካኝነት የሚፈጸሙ ክፍያዎችን ወጥና ተናባቢ በማድረግ አንዱ የሌላኛው መጠቀም የሚያስችል "ኪው አር ኮድ" ይፋ መሆኑን ነው የገለጹት።

ይህም አንድ ግለሰብ የየትኛውም ባንክ ደንበኛ ወይም የሞባይል ዋሌት ተጠቃሚ ቢሆንም ክፍያውን በ"ኪው አር ኮድ" እርስ በርስ በማናበብ መክፈል እንደሚቻል ተጠቅሷል።        

እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ ተናባቢ "ኪው አር ኮድ" ዜጎችም ደንበኛ በሆኑበት የፋይናንስ ተቋም ያገኙትን "ኪው አር ኮድ" በእጅ ስልክ በማስነበብ የትኛውንም ዓይነት ክፍያ መፈጸም የሚያስችላቸው የአገልግሎት ሥርዓት ነው።

ደንበኞች በ"ኪው አር ኮድ" ክፍያ በሚፈጽሙበት ወቅት የደንበኛ ስም፣ የሒሳብ ቁጥር፣ የባንክ አድራሻና የግብር ከፋይ መለያ በአንድ ቦታ በቀላሉ በማስነበብ ክፍያን መፈጸም እንደሚያስችል ተናግረዋል። 

ዜጎችም የትኛውንም ዕቃና አገልግሎት ግዥ ሲፈጽሙ የንግድና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በሚያስቀምጡት "ኪው አር ኮድ" አማካኝነት ክፍያን በቀላሉ መፈጸም ያስችላቸዋል ብለዋል።

ይህም በንግድ ሥርዓቱ ላይ የሚፈጸመውን የጥሬ ገንዘብ ክፍያ በእጅ ስልክ የዲጂታላይዝ ሥርዓት በመተካት ፈጣንና ቀልጠፋ አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል ገልፀዋል።


 

የኢትስዊች አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ይላበስ አዲስ፤ የፋይናንስ ተቋማት በተናጠል የሚሰጡበትን የተበታተነ አገልግሎት ወጥና ተናባቢ የሆነ የ"ኪው አር ኮድ" ይፋ በማድረግ ዜጎች ቀላል ክፍያ የሚፈጽሙበት ምኅዳር መፈጠሩን ተናግረዋል።

በንግድ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በሚቀመጡ ፖስ ማሽን፣ የክፍያ ካርድ፣ በሞባይል ባንኪንግ፣ በሲቢኢ ብር ዋሌት፣ አሊያም በሽያጭ መሳሪያ ክፍያ የሚፈጸምባቸው አገልግሎቶች ከፍተኛ ዋጋን እንደሚጠይቁ አንስተዋል።

የ"ኪው አር ኮድ" ግን በዝቅተኛ ወጪ በማንኛውም የንግድ ድርጅትና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በቀላሉ በማስቀመጥ ደንበኞች በቀላሉ በእጅ ስልካቸው አንብበው መፈጸም ይችላሉ ብለዋል።

የ"ኪው አር ኮድ" በቀላል ወጪና በብዙ እጥፍ በማባዛት ዜጎች በታክሲ፣ በጫማ ፅዳትና ዕድሳትን ጨምሮ ከቀላል እስከ ከፍተኛ የክፍያ አገልግሎት መፈጸም እንደሚችሉ አስታውቀዋል።

በኢትስዊችና በብሔራዊ ባንክ ትብብር ማንኛውም የፋይናንስና የንግድ ተቋም እንዲሁም ተገልጋይ በ"ኪው አር ኮድ" አማካኝነት ቀላል ክፍያ የሚፈጸምበት ሥርዓት መፈጠሩ ተገልጿል።

ባለፈው ሳምንት የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምሕረቱ ጨምሮ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም የሥራ ኃላፊዎችና ተወካዮች በተገኙበት የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም