በኢትዮጵያ የመረጃና ደኅንነት ዘርፍ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረከቱት ዶክተር አስማማው ቀለሙ ስርዓተ ቀብር ተፈፀመ

117


አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 8/2016(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ የመረጃና ደኅንነት ዘርፍ  ውስጥ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረከቱት ዶክተር አስማማው ቀለሙ ስርዓተ ቀብር በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈፀመ።

ከ1956 ዓ.ም ጀምሮ ለ60 ዓመታት ያህል በመረጃና ደኅንነት ዘርፍ ያገለገሉት ዶክተር አስማማው ቀለሙ ባደረባቸው ህመም በሀገር ውስጥና በውጭ በህክምና ሲረዱ ቆይተው ሚያዝያ 5ቀን 2016 ዓ.ም በተወለዱ በ84 ዓመታቸው ህይወታቸው አልፏል።

ዶክተር አስማማው ቀለሙ በሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ከማገልገል በተጨማሪ የሀገር ዉስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል።

ዶክተር አስማማው ቀለሙ በኢኮኖሚክስ የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከእስራኤል ሀገር፣ የሦስተኛ ድግሪያቸውን ከቡልጋሪያ ካርል ማርክስ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኢኮኖሚክስ እንዲሁም ፖስት ዶክትሬታቸውን እንግሊዝ ሀገር ከሚገኘው ለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ አግኝተዋል። 

ከእነዚህም በተጨማሪ በፖሊስነት ህይወታቸው የ9ኛ ኮርስ አባል የነበሩ ሲሆን የኮለኔልነት ማዕረግ ላይ ደርሰዋል።

ዶክተር አስማማው ቀለሙ በድህረ የኢትዮ- ሶማሊያ ጦርነት በሶማሊያ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር በመሆን በሁለቱ ሀገራት መካከል ሠላም እንዲሰፍን እና የእስረኞች ልውውጥ እንዲደረግ የአንበሳውን ድርሻ ተጫውተዋል። 

ዶክተር አስማማው ቀለሙ በቀጠናው የኢትዮጵያን ጂኦ-ስትራቴጂካዊ ጥቅም ለማስጠበቅ እልህ አስጨራሽ ትግል በማድረግ የሚታወቁ ታላቅ የመረጃና ደኅንነት ባለሙያ ነበሩ።

የመረጃና ደኅንነት ሙያን በተመለከተ በእስራኤል እና በጀርመን የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመከታተል እና ሙያዊ እውቀትን፣ ክህሎትን፣ አስተሳሰብን እና ስብዕናን መሰረት አድርጎ አሻጋሪ ተቋም በሀገር ውስጥ እንዲገነባ በ1974 ዓ.ም የስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩትን በማቋቋም ከፍተኛ አስተዋጾ አድርገዋል።

በአጼ ኃይለ ሥላሴ እና በደርግ ዘመነ መንግስት የኢትዮጵያን ጥቅም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ ከፍተኛ ስራ የሰሩት ዶክተር አስማማው ቀለሙ በኢህአዴግ ዘመን ለ12 ዓመታት በእስር ቤት እንዲያሳልፉ መደረጋቸው ይታወቃል፡፡

በእስር በቆዩባቸው ዓመታትም ታራሚዎች የትምህርት እድል እንዲያገኙ እና ትምህርት እንዲስፋፋ በማድረግ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል። 

ከእስር ከወጡ በኋላም ዘመን ባንክን ጨምሮ በተለያዩ የግል ተቋማት በአማካሪነት እና ኃላፊነት አገልግለዋል።

ዶክተር አስማማው ቀለሙ ከ2010 ዓ.ም ሀገራዊ ለውጥ በኃላ በተደረገላቸው ተቋማዊ ጥሪ መሰረት የጤና መታወክ እስካጋጠማቸው ታህሳስ 2016 ዓ.ም ድረስ በብሔራዊ ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ በማስተማር ላይ የነበሩ ሲሆን በተለያዩ ሚዲያዎች በመቅረብ በተለያዩ ወቅታዊ ሀገራዊ፣ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ የደኅንነት፣ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ በሳል ትንታኔ በመስጠት ሀገራዊ ኃላፊነታቸዉን በታማኝነት እና በቅንነት ተወጥተዋል። 

ዶክተር አስማማው ቀለሙ የሀገር ብሔራዊ ጥቅም እና ደኅንነት የማስጠበቅ ስራ ከወገንተኝነት የጸዳ፣ የእድሜ ልክ እና በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ቅድሚያ የሚሰጠው ሥራ መሆኑን በተግባር ያሳዩ ባለሙያ ነበሩ።

ዶክተር አስማማው ቀለሙ ባለትዳር እና የሦስት ወንድ ልጆች አባት ነበሩ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም