ኮሚሽኑ በወረዳ ደረጃ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ወክለው በምክክር ሂደቱ የሚሳተፉ ተወካዮች ልየታ እያካሄደ ነው

212

ሀዋሳ ፤ሚያዚያ 8/2016(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሻሸመኔ ክላስተር  በወረዳ ደረጃ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ወክለው በምክክር ሂደቱ የሚሳተፉ ተወካዮች ልየታ እያካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ በኮሚሽኑ የኦሮሚያ ተሳታፊ ልየታ ቡድን አስተባባሪ አቶ ብዙነህ አስፋ ለኢዜአ እንደገለጹት በኮሚሽኑ ዕቅድ መሰረት በክልሉ በምክክር ሂደቱ የሚሳተፉ ተወካዮች ልየታ እየተካሄደ ይገኛል።


 

በኦሮሚያ ክልል የማህብረሰብ ክፍሎች ተወካዮች ልየታ በአራት ክላስተር ተከፍሎ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው የዛሬው የሻሸመኔው ክላስተር የመጨረሻው ዙር መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም በምክክር ሂደቱ የሚሳተፉ ተወካዮች ልየታ መድረክ ላይ ከምስራቅ ጉጂ ዞን 11 ወረዳዎች የተውጣጡ ከ 1 ሺህ በላይ የተለያዩ ህብረተሰብ ወኪሎች እየተሳተፉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት በመድረኩ የሀገራዊ ምክክር ምንነትና አስፈላጊነት እንዲሁም የአመራረጥ ሂደቱን በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለጻና ማብራሪያ  ለተሳታፊዎች እየተሰጠ ነው።

የመድረኩ ዓላማ በሀገር አቀፍ ምክክሩ ላይ የሚሳተፉ ግለሰቦች “ልየታ” አካታች እና አሳታፊ እንዲሁም ሂደቱ ሁሉም የተስማማበት እና ተዓማኒነት ያለው እንዲሆን ለማስቻል መሆኑን አስረድተዋል።

በሻሸመኔ ከተማ ዛሬ የተጀመረው በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተወካዮችን የማስመረጥ ሂደት እስከ ሚያዚያ 11 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚቆይ አመላክተዋል።

እንደ አቶ ብዙነህ ገለፃ በሻሸመኔ ክላስተር ውስጥ የተካተቱ ዞኖች ባሌ፣ምስራቅ ባሌ፣ ቦረና፣ ምስራቅ ቦረና፣ ጉጂ እና ምስራቅ ጉጂ  ናቸው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም