መንግሥት የዳታ ማዕከላት ግንባታ ላይ የሚሰማሩ ኢንቨስተሮች የሚያደርገውን እገዛ አጠናክሮ ይቀጥላል - የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር

191

 አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 8/2016(ኢዜአ)፡-  የዳታ ማዕከላት ግንባታ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሥራን የሚደግፍ በመሆኑ መንግሥት በዘርፉ ለሚሰማሩ ኢንቨስተሮች የሚያደርገውን እገዛ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለፀ።

ዊንጉ አፍሪካ በኢትዮጵያ የገነባው የግል ዳታ ማዕከል ታየር-3 የምስክር ወረቀት ማግኘቱን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

ዊንጉ አፍሪካ በአይ ሲቲ ፓርክ የገነባው የዳታ ማዕከል ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሆኖ በመገኘቱና እያደገ የሚመጣውን የደንበኞቹን ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችል መሠረተ-ልማት በመገንባቱ ነው ታየር-3 የምስክር ወረቀት "ከአፕታይም" ከተሰኘው ዓለም አቀፍ ኢንስቲትዩቱ ያገኘው ተብሏል። 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታው ይሽሩን አለማየሁ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እያደረገች ላለችው ጉዞ መረጃ ወሳኝ ነው።

መረጃ ደኅንነቱ ተጠብቆ መቀመጥና አስፈላጊ በሆነበት ሰዓት መገኘት ያለበት መሆኑን አንስተው፤ መንግሥት ተጨማሪ የዳታ ማዕከላት እንዲገነቡ ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል።

አሁን ላይ በኢትዮጵያ ዊንጉ አፍሪካ፣ ኢትዮ-ቴሌኮምና ሌሎች ተቋማት የዳታ ማዕከላት መገንባታቸውን ጠቅሰው፤ ተጨማሪ የዳታ ማዕከላት እንዲገነቡ ፍላጎት መኖሩን ጠቅሰዋል።

የዳታ ማዕከላት ግንባታ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሥራን የሚደግፍ በመሆኑ መንግሥት በዘርፉ ለሚሰማሩ ኢንቨስተሮች እገዛ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

በዊንጉ አፍሪካ የተገነባው መሠረተ-ልማት እውቅና ማግኘቱ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን አቅም የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዳታ ማዕከሉ የእውቀት ሽግግር እንዲሁም የሥራ ዕድል በመፍጠር ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።


 

የዊንጉ አፍሪካ ቺፍ ስትራቴጂ ኦፊሰር ኒኮላስ ሎጂ በበኩላቸው፤ በአይ ሲቲ ፓርክ የተገነባው ዳታ ማዕከል መሠረተ-ልማት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑ ለእውቅና እንዳበቃው ገልፀዋል።

እውቅናው ደንበኞች መረጃቸውን ሲያስቀምጡ ደኅንነቱ ጥበቃ ላይ መተማመን እንዲፈጠርላቸው የሚረዳ መሆኑን ጠቁመዋል።

እውቅናውን የሰጠው "አፕታይም" የተሰኘው ተቋም ከ140 በላይ ለሆኑ አገራት እውቅና መስጠቱን አንስተው፤ ድርጅታቸው በኢትዮጵያ የገነባው ዳታ ማዕከል እውቅና ማግኘቱ ኢትዮጵያን ከእነዚህ አገራት መካከል እንድትካተት ያስቻላት ነው ብለዋል።

ይህም አገሪቱ የያዘችውን የዲጂታል 2025 ስትራቴጂ ለማሳካት የሚያግዝ መሆኑን በመግለጽ።

ዊንጉ አፍሪካ በኢትዮጵያ በቀጣይም ሌሎች ኢንቨስትመንቶችን እንደሚያከናውን ጠቁመው፤ ባገኘው እውቅና ኩራት እንደሚሰማውም ተናግረዋል።

ዊንጉ አፍሪካ ግሩፕ በ50 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በአዲስ አበባ አይ ሲቲ ፓርክ ያስገነባውን ዘመናዊ የዳታ ማዕከል የዛሬ ዓመት ገደማ ነበር ያስመረቀው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም