በአዳማ ከተማ የሌማት ትሩፋት ተሳታፊዎች በወተትና እና እንቁላል ምርት ከራሳቸው ፍጆታ ባለፈ ለገበያ መረጋጋት አስተዋጾ እያደረጉ ነው

አዳማ፤ ሚያዚያ 8/2016(ኢዜአ)፡- በአዳማ ከተማ የሌማት ትሩፋት መርሀግብር ተሳታፊዎች በወተትና እና እንቁላል ምርት ከራሳቸው ፍጆታ ባለፈ ለገበያ መረጋጋት አስተዋጾ እያደረጉ መሆኑን የከተማው ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በከተማው በመርሀግብሩ ከ350 ሺህ በላይ እንቁላል በየቀኑ ለገበያ እየቀረበ መሆኑንም ጽህፈት ቤቱ ገልጿል።       

በጽህፈት ቤቱ የእንስሳት ሀብት ልማት ቡድን መሪ አቶ አብተው ለማ ለኢዜአ እንደገለጹት በከተማዋ የሌማት ትሩፋትና የከተማ ግብርናን ለማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

ለእዚህም ከምስራቅ ሸዋ ዞን አዳማ ወረዳ ወደ አዳማ ከተማ በተጠቃለሉ 28 ቀበሌዎች ላይ የዶሮ እርባታ፣ የወተትና የሥጋ እንስሳት ልማት እንዲሁም የንብ ማነብ እና የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ በአዳማ ከተማ ስድስት ክፍለ ከተሞችና የተለያዩ ወረዳዎች የሌማት ትሩፋት መርሀግብር ውጤታማ በሆነ መንገድ በመተግበር ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዶሮ አርባታ፣ ለሥጋና ለወተት ላሞች ልማት፣ እንዲሁም ለንብ ማነብ ሥራ የሚሆኑ ከ1ሺህ 285 በላይ ማዕከላት በባለሃብቶች፣ በህብረተሰቡ እና በከተማ መስተዳደሩ ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውንም አቶ አብተው ገልጸዋል።


 

ለማዕከላቱ ግንባታ በጥሬ ገንዘብ፣ በመሬት አቅርቦት እና በጉልበት ከ5 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ካፒታል ሥራ ላይ ውሏል።

የሌማት ትሩፋቱ  ከቤት ውስጥ ፍጆታ ባለፈ በየዕለቱ ከ350ሺህ በላይ እንቁላል ለገበያ እየቀረበ መሆኑን አቶ አብተው ገልጸው፣ ይህም በከተማው የአንድ እንቁላል ዋጋ ከ12 ብር ወደ 8 ብር ዝቅ እንዲል ማድረጉን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የወተት ምርትን ለማሳዳግ በተሰራው ሥራ 80 ብር የነበረው የአንድ ሊትር ወተት ወደ 60 ብር መውረዱን ገልጸዋል። 

"የሌማት ትሩፋት መርሀግብሩን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የተገነቡ ማዕከላትን በሙሉ አቅም ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ ነው" ብለዋል 

አቶ አብተው ጨምረው እንዳሉት በማዕከላቱ በእንስሳት፣ በዶሮ፣ በንብ ማነብ እና በአሣ እርባታ ልማት ከ25ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ እድል ተፈጥሯል።

በከተማው ስድስት ክፍለከተሞችም 10 የእንቁላልና የወተት ምርት መሸጫ ማዕከላት እየተገነቡ ሲሆን የአራቱ የገበያ ማዕከላት ግንባታም መጠናቀቁን ተናግረዋል።

በከተማው የሌማት ትሩፋት መርሀግብር ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል የደካ አዲ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር  ግርማ ያሚ በተሰማሩበት ዘመናዊ የወተት ላሞች እርባታ ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ሰባት የወተት ላሞችን በማለብ የሚያገኙትን ወተት ከቤት ፍጆታ ባለፈ በቀን እስከ 100 ሊትር ወተት ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በየቀኑ የሚያገኙትን የወተት ምርት 150 ሊትር ለማድረስ ጠንክረው እየሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

እየተገነቡ ያሉ የምርት መሸጫ ማዕከላት የወተትና የወተት ተዋፅዖ ምርታቸውን ለከተማዋ ህብረተሰብ በአንድ ቦታ ለማቅረብ እንደሚያስችላቸውም ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ከ15 በላይ የወተት ላሞችን እያረቡ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ጥጆቹን ለአካባቢው አርሶ አደሮች በመሸጥ ገቢ እያገኙ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በዶሮ እርባታ የተሰማሩት አቶ ሹሚ ረጋሳ የሌማት ትሩፋት መርሀግብር የእንቁላል ምርታቸውን ከቤት ፍጆታ ባለፈ ለገበያ ለማቅረብ እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።

በእዚህም በገበያው የዋጋ መረጋጋት ታይቷል ያሉት አቶ ሹሚ፣ ሥራውን ሲጀምሩ አንድ እንቁላል ከ12 እስከ 15 ሺህ ብር ይሸጥ የነበረው በአሁኑ ወቅት ስምንት ብር መሸጡን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ዘመናዊ የንብ ቀፎዎችን በማምረት ለተጠቃሚዎች እያቀረበ ያለው ወጣት ፀጋዬ ሃሌሌ በበኩሉ፣ የሌማት ትሩፋት በሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ እንዳደረገው ተናግሯል። 

አዳማ ከተማን ጨምሮ ለምስራቅ ሸዋ ዞን አምስት ወረዳዎች ዘመናዊ የንብ ቀፎ ሰርቶ ለማቅረብ በገባው ውል መሰረት በአሁኑ ወቅት ምርቱን እያቀረበ መሆኑን ገልጿል።

በሥራውም ከራሱ በተጨማሪ ለ22 ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ወጣት ፀጋዬ ተናግሯል። 

 

     

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም