የሐረሪዎች የጥበብና የእውቀት ውጤቶች ድንበር ተሻግረው የዓለማችን ህዝቦች የቅርስ ሀብት ሆነዋል - አቶ ቀጄላ መርዳሳ

88

ሐረር ፤ ሚያዝያ 08/2016 (ኢዜአ)፡- የሐረሪዎች የጥበብና የእውቀት ውጤቶች ድንበር ተሻግረው የዓለማችን ህዝቦች የቅርስ ሀብት ሊሆኑ በቅተዋል ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ ተናገሩ።

በሐረሪ ክልል የሸዋል ኢድ በዓል የመክፈቻ መርሃ-ግብር ተካሂዷል።

በመርሃ-ግብሩ ላይ  የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ የሐረሪዎች የጥበብና የእውቀት ውጤቶች ድንበር ተሻግረው የዓለማችን ህዝቦች የቅርስ ሀብት መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

ሐረሪዎች ከደማቅ ታሪኮቻቸው ጎን ለጎንም የሰላምና የፍቅር ተምሳሌት ናቸው ሲሉም ገልጸዋል።

በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበው የሸዋል ኢድ በዓል "የፍቅር በዓል ነው" ያሉት ሚኒስትሩ፤ በዚህም እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉም ገልጸዋል።


 

አኩሪ ባህሎቻችንና ቅርሶቻችንን በመንከባከብ፣ በመጠበቅና ለትውልድ ለማስተላለፍ በሚከናወኑ ስራዎች ላይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ መስራት ይጠበቅበታል ሲሉም አስገንዝበዋል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የቱሪዝም ሃብቶች ባለቤት ናት፤ ለቱሪዝም ልማትም እምቅ አቅም አላት ያሉት ደግሞ የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ናቸው።


 

ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ማጎልበት ወሳኝ መሆኑን የጠቆሙት አምባሳደሯ በዚህም መንግስት የቱሪዝም ዘርፉን ከእድገትና ብልጽግና መሰረቶች መካከል አንዱ በማድረግ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ለቱሪዝም ፍሰቱ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ መሰረተ ልማቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከክልሉ ጋር የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በወቅቱ እንዳሉት የሸዋል ኢድ በዓል የሐረሪ ህዝብ ከሌሎች ወንድም እህቶቹ ጋር በመሆን በአብሮነት የሚያከብረው ነው። 


 

በዓሉ በዓለም በማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገቡ ትልቅ ስኬት በመሆኑ ለመላው የአገሪቱ ህዝቦች እንኳን ደስ አለን ብለዋል።

ሸዋል ኢድ በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ ከሐረሪዎች ፌስቲቫልነት ባለፈ ለመላው ኢትዮዽያውያን ብሎም የመላው የዓለም ህዝብ እሴት፣ ክዋኔ፣ ባህልና ልዩ ወጎች የሚንጸባረቅበት መስተዋት አካል ማድረጉንም አመልክተዋል።


 

በጀጎል ዙርያና በጀጎል ውስጥ በመንግስትና በግል ተቋማት እንዲሁም በህዝብ ተሳትፎ የተከናወኑ ስራዎችም ተስፋ ሰጪ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በስነ ስርዓቱ ላይ የሸዋል ኢድ በዓል በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ፣ ትምህርት እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም በማይዳሰስ ቅርስነት እንዲመዘገብ አስተዋጽዎ ላበረከቱ ለፌዴራል፣ለክልል ተቋማትና ባለ ድርሻ አካላት እውቅና ተሰጥቷል።

"ሸዋል ኢድ ለህብረ ብሔራዊ አንድነታችንና ለቱሪዝም እድገታችን" በሚል መሪ ሐሳብ የተዘጋጀው የባህል ዐውደ ርዕይና ፌስቲቫል መከፈቱ ይታወሳል።

እንዲሁም የ"ጌይ ከሎይታ"  ውይንም  "የሐረሪ ባህላዊ ቆብ"  ብራንድ በአዕምሯዊ ቅርስነት የተመዘገበበት የምስክር ወረቀት ርክክብ ተካሂዷል።

በበዓሉ ላይ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችን ጨምሮ ሌሎች እንግዶች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም