በክልሉ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የህዝብን ተጠቃሚነት ለሚያሳድጉ ተግባራት ትኩረት ተሰጥቷል-- አቶ እንዳሻው ጣሰው

226

ሆሳዕና፤ ሚያዝያ 8/2016(ኢዜአ)፡- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የህዝብን ተጠቃሚነት ለሚያሳድጉ ተግባራት ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ገለጹ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ እንዳሻው ጣሰው ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት በክልሉ ባለፉት ወራት በተለያየ መስክ የተከናወኑ ተግባራትን በመገምገም ቀጣይ የሚሰሩትን ለይቶ ወደሥራ ተገብቷል።

በተለይም በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የህዝብን ተጠቃሚነት ለሚያሳድጉ ተግባራት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ወደሥራ መገባቱን ገልጸዋል።

በትምህርት፣ በጤናና ግብርና ዘርፎች እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን ለአብነት የጠቀሱት አቶ እንዳሻው፣ በትምህርት ዙሪያ ባለፈው ዓመት በብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና የገጠመውን የውጤት ማሽቆልቆል ችግር ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለዚህም የትምህርት ቤቶች ደረጃን በማሻሻል ለመማር ማስተማር ሥራው ምቹ ከማድረግ ጎን ለጎን 10 ሺህ መምህራንና ርዕሰ መምህራን በኢዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ትግበራ ላይ ስልጠና አግኝተው ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን አመልክተዋል።

በጤናው ዘርፍም የጤና ተቋማትን ከማስፋፋት ባለፈ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ህዝቡ የሚያነሳቸውን ችግሮች ለመፍታት ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በክልሉ የማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎትን በማጠናከር በርካቶችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም አቶ እንዳሻው ተናግረዋል።

ገበያ በማረጋጋት፣ ለምሩቃን የሥራ ዕድል በመፍጠር እና በኢንቨስትመንት ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

እንደ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ የግብርናን ውጤታማነት ለማጠናከር ለመስኖ ልማትና ለሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

ክልሉ ለም መሬትና የውሃ አማራጭ እንዳለው ያነሱት አቶ እንዳሻው፣ በዘርፉ እየተመዘገበ ያለውን  አመርቂ ውጤት ለማጠናከር ትኩረት መሰጠቱንም ገልጸዋል።

በመሰረተ ልማት በተለይ የመንገድ ልማት ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ካለው አበርክቶ አንጻር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት አቶ እንዳሻው፣ በዚህም የዞን፣ ወረዳና ቀበሌ ተደራሽ መንገዶች ግንባታና ዕድሳት ሥራዎች ይከናወናሉ ብለዋል። 

በክልሉ የመንገድ መሰረተ ልማቶችን ለማጠናከር እየተሰሩ ባሉ ሥራዎች የህብረተሰቡ ተሳትፎ ጠንካራ መሆኑን ገልጸው፣ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን ተደራሽነት ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ የህዝብን የልማት ጥያቄዎች ለመፍታት እየተደረገ ላለው ስራ ስኬታማነት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም አቶ እንደሻው ጠይቀዋል።

የህዝብ የልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት ክልሉ ገቢን በአግባቡ ለመሰብሰብ አቅዶ በንቅናቄ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በክልሉ በቀጣይ ወራት ለማከናወን የተለዩ የልማት ሥራዎችን በተሳካ መልኩ ለማከናወን የሀብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ በየአካባቢው ለልማት ሥራዎች ስኬታማነት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም