የዞኑን የውሃ ሃብት ለግብርና ልማት ማዋል የሚያስችል የመሰረተ ልማት ስራ እየተከናወነ ነው

117

መቱ ፤ ሚያዚያ 8/2016(ኢዜአ)፡- በዞኑ የሚገኘውን የውሃ ሃብት ለግብርና ልማት ማዋል የሚያስችል የዘመናዊ መስኖ መሰረተ ልማት ማስፋፋት ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የኢሉባቦር ዞን የመስኖ ልማት ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

የዞኑ የመስኖ ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ደመቁ ተረፈ እንደገለፁት፤ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ወረዳዎች ወደ ስራ የገቡ ዘጠኝ የመስኖ መሰረተ ልማት ስራዎች ግንባታ በትኩረት እየተከናወነ ነው።

ዞኑ ካለው እምቅ የውሃ ሃብት አቅም አንፃር አሁን ያለው የመስኖ ልማት በቂ አለመሆኑን ያነሱት ወይዘሮ ደመቁ አርሶ አደሩን ከዝናብ ጠባቂነት በማላቀቅ ዓመቱን ሙሉ ማልማት የሚያስችላቸውን ሁኔታ ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በተለይ የስንዴ፣ የሩዝና ሌሎች ፕሮግራሞችን ሙሉ በሙሉ በመተግበር የምግብ ዋስትናና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ዘርፉን ይበልጥ ለማስፋፋት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በዞኑ 100ሺህ ሔክታር መሬትን በመስኖ ማልማት መቻሉን ገልጸው እየጨመረ የመጣውን ፍላጎት ማርካት የሚያስችሉ ሁለት የመስኖ ፕሮጀክቶች በ400 ሚሊዮን ብር እየተገነቡ ነው ብለዋል።

በአልጌ ሳቺ ወረዳ በሴሴ ወንዝና በዳሪሙ ወረዳ እየተገነቡ የሚገኙት የመስኖ ፕሮጀክቶቹ በተያዘው ዓመት እንደሚጠናቀቁና ወደ ስራ ሲገቡም 2ሺህ ሔክታር መሬትን እንደሚያለማ አመልክተዋል።

የአልጌ ሳቺ ወረዳ ነዋሪው አቶ ዲዳ ነቤ ፕሮጀክቱ በባሕላዊ መልክ ያከናውኑ የነበረውን የመስኖ ልማት በማዘመን ተጠቃሚነታቸውን እንደሚያሻሽል ተስፋ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

የመስኖ ፕሮጀክቱ ቀጣይነት ያለው ልማትን ከማረጋገጥ ባለፈ ለስራ አጥ ወጣቶች የስራ ዕድልን እንደሚፈጥርም ገልፀዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ቡጡሻ ታዬ በበኩላቸው የመስኖ ፕሮጀክቱ የዝናብ ወቅትን ብቻ ጠብቀው ከማረስ እንዲላቀቁና በአካባቢያቸው የሚገኘውን የውሃ ሀብት ለልማት ለማዋል እንደሚያስችላቸው አንስተዋል።

ይህም ጊዜያቸውን ያለ ስራ ከማሳለፍ እንደታደጋቸውና በአግባቡ እንዲጠቀሙበት እንደሚያስችላቸው ገልፀዋል።

በዘመናዊ መልኩ ውሃን ለመስኖ ልማት መጠቀም የሚያስችል ስራ በወረዳቸው እየተከናወነ መሆኑ ለስራ ባህል መሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን የገለፁት ደግሞ የአለም ሳቺ ወረዳ ነዋሪው አቶ ጀማል ፈቃዱ ናቸው።

ዝናብን ጠብቀው በዓመት አንዴ ብቻ የሚያርሱበትንም ሁኔታ የሚቀይርላቸው በመሆኑ የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውንም እንደሚያሻሽል ተናግረዋል።

የሁሩሙና የአልጌ ሳቺ ወረዳዎች ነዋሪዎቹ ሲሳይ እምሩና አርሶ አደር ብርሃኑ አብዲሳ በየወረዳዎቻቸው በተሰሩ የመስኖ ልማት ግንባታ ስራዎች በዓመት ሁለትና ከዚያ በላይ ጊዜ በማምረት ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ገልፀዋል።

የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶቹ የበጋ ስንዴን ጨምሮ እንደ በቆሎ ያሉ ሌሎች ሰብሎችን በማፈራረቅ ለማልማት የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸውም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም