በክልሉ የአርብቶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል የሚያግዙ መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቷል - አቶ ማስረሻ በላቸው 

104

ሚዛን አማን ፤ ሚያዚያ 8/2016(ኢዜአ)፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የአርብቶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል የሚያግዙ መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቷል ሲሉ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ገለጹ።

የክልሉ አርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢዎች ጉዳይ ቢሮ የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በክልሉ በቆላማ አካባቢዎች ለሚኖሩ አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሮች የመሠረተ ልማት እና የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስንነት መኖሩን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የእነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች ኑሮ ለማሻሻል ክልሉ የመሰረተ ልማት ችግሮቻቸውን መፍታት ቀዳሚ ተግባር አድርጎ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም በቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት 57 ቀበሌዎችን በማቀፍ በመንገድ መሠረተ ልማት፣ በትምህርት ቤት፣ በጤና ኬላ ግንባታ እንዲሁም በመኖ ልማት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን አንስተዋል።

ለእነዚህ አካባቢዎች በተሰጠው ትኩረት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ውጤት እየተገኘባቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የክልሉ መንግስት ለቆላማ አካባቢ ነዋሪዎች ህይወት መሻሻልና መለወጥ የተቀረጹ ፕሮጀክቶችን ከመደገፍ ባለፈ አስፈላጊውን ክትትል እያደረገ መሆኑን አቶ ማስረሻ ተናግረዋል።


 

የክልሉ አርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢዎች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ታምሩ ቦኒ በበኩላቸው በአርብቶ አደር አካባቢዎች ላይ የሚስተዋለውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ቢሮው በትኩረት ይሠራል ብለዋል።

መንግስት ያልደረሰባቸውን የልማት ክፍተቶች ለማገዝ እየሰሩ ያሉ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ውጤታማ ለማድረግ በቢሮው በኩል አስፈላጊው ትብብር እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል። 

"በተለይ የአገልግሎት መስጫ መሠረተ ልማቶች ግንባታ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ያሉት አቶ ታምሩ፣ የተጠናቀቁትን ተረክቦ ማስተዳደር ላይ የክልሉ ሴክተር ተቋማት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።


 

በቢሮው የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ደረጀ በቀለ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በመኤኒት ጎልዲያ፣ መኤኒት ሻሻ እና ሱሪ ወረዳዎች ከ22 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የእንስሳት መኖ የማልማት ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።

በመሰረተ ልማትም ጋቺት ወረዳን ከመኤኒት ጎልዲያ ጋር ለማገናኘት የዳል ወንዝ ድልድይን በመገንባት ከ16 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ ከ237 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዞ የተለያዩ የኑሮ ማሻሻያ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፣ አራት የጥልቅ ጉድጓድ ውሃ ቁፋሮ ሥራም እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

አስተባባሪው እንዳሉት ባለፉት ሦስት ዓመታት 10 የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ አምስት ጤና ኬላ እና ሁለት የእንስሳት ሕክምና ክሊኒክ ተገንብተዋል።

በአሁኑ ወቅትም ሦስት ትምህርት ቤቶች በግንባታ ሂደት ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

በውይይት መድረኩ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ መሆናቸውም ታውቋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም