በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮ የበልግ እርሻ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ማልማት ተጀመረ

123

ሮቤ ፤ ሚያዝያ 8/2016(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮ የበልግ እርሻ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች የማልማት ሥራ መጀመሩን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ። 

የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹና ሌሎች የክልሉ መንግስት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የዘንድሮ የበልግ እርሻ ሥራ በባሌ ዞን ሲናና ወረዳ ተጀምሯል። 

የቢሮው ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፣ በዘንድሮው የበልግ እርሻ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች የማልማት ሥራ እየተካሄደ ነው። 

ልማቱ በአብዛኛው ሜካናይዜሽንን ጨምሮ ሌሎች የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ እየለማ መሆኑን አክለዋል። 

የዘንድሮው የበልግ አዝመራ ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግም ከ4 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ተናግረዋል። 

በዲጂታልግብይት የተካሄደው የአፈር ማደበሪያ ሽያጭ አርሶ አደሩ ግብዓቱን በወቅቱ እንዲያገኝ ከማድረጉም በተጓዳኝ ይታይ የነበረውን ህገ ወጥነት የሚያስቀር እንደሆነ ተናግረዋል። 

አቶ ጌቱ እንዳሉት፣ በክልሉ ዘንድሮ የበልግ፣ የመኸርና የበጋ መስኖ ልማት ሰፊ መሬት በተለያዩ የሰብል ዘሮች ለማልማት ታቅዷል። 

የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አልይ መሐመድ በበኩላቸው በዞኑ በዘንድሮው የበልግ እርሻ ከ221 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የሰብል ዘሮች  የማልማቱ ሥራ እየተከናወነ ነው።

ከሲናና ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል አቶ በቀለ ከተማ በሰጡት አስተያየት፣ በዘንድሮው የበልግ ወቅት የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን በመጠቀም የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ገልፀዋል። 

በዘንድሮው የበልግ ወቅት የግብርና ግብዓቶች በወቅቱ መቅረባቸው የዘር ወቅቱን ውጤታማ እንደሚያደርግ የገለጹት ደግሞ ሌላኛው የወረዳው ነዋሪ አርሶ አደር ታደሰ አበበ ናቸው። 

አርሶ አደሩ በአሁኑ ወቅት የማሳ ዝግጅት አጠናቀው በአካባቢው መጣል በጀመረው የበልግ ዝናብ ተጠቅመው በኩታ ገጠም እያለሙ መሆኑን ተናግረዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም