በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚዎች ምጣኔ 52 በመቶ ደርሷል - የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚዎች ምጣኔ 52 በመቶ ደርሷል - የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 8/2016(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚዎች ምጣኔ 52 በመቶ መድረሱን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ኢትዮጵያ ከውሃ፣ ከፀሐይ፣ ከነፋስ፣ ከከርሰ-ምድር ሙቀትና እንፋሎት ጂኦ-ተርማል፣ ባዮማስ ከእንስሳትና እጽዋቶች ተረፈ-ምርት የሚገኝ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም አላት።
መንግሥት ባዘጋጀው የአሥር ዓመት የመሪ ልማት ዕቅድ በኢነርጂው ዘርፍ የኤሌክትሪክ አቅርቦትና ተደራሽነት ማሳደግ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለመስጠትን ትኩረት አድርጓል።
በዕቅዱ የኢትዮጵያን የኃይል ማመንጨት አቅም ከ4ሺህ 478 ሜጋ ዋት ወደ 19ሺህ 900 ሜጋ ዋት ከፍ ለማድረግ ታልሟል።
በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ደንበኞችን ከ5 ነጥብ 8 ሚሊየን ወደ 24 ነጥብ 3 ሚሊየን ለማሳደግም ዕቅድ ተይዟል።
በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ለማስፋት የተለያዩ ፕሮጀክቶች እና መርሃ-ግብሮች ተቀርፀው እየተተገበሩ የሚገኝ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የብሔራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ነው።
ይህ ፕሮግራም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2017 ጀምሮ እየተተገበረ የሚገኝ ሲሆን፤ ማሻሻያዎች የተካተቱበት የመርሃ-ግብሩ ሰነድ እ.አ.አ በ2019 ይፋ ተደርጎ እየተሰራበት ይገኛል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ(ዶ/ር)፤ የኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ዋነኛ ዓላማ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2030 ስድሳ አምስት(65) በመቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከብሔራዊ የኃይል ቋት እንዲሁም ቀሪው 35 በመቶ ከኃይል ቋት ውጭ ባሉ ቴክኖሎጂዎች ተደራሽ ማድረግ መሆኑን ለኢዜአ ገልፀዋል።
ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በመጀመሪያው ምዕራፍ የፕሮግራሙ ትግበራ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ከዕቅዱ በላይ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።
በፕሮግራሙ አፈጻጸም ላይ አበረታች ውጤቶች ቢታዩም ለመርሃ-ግብሩ አፈጻጸም የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገቡ የተለያዩ አካላት ድጋፍ እያደረጉ እንደማይገኝ አመልክተዋል።
ለመርሃ-ግብሩ ተፈጻሚነት 6 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልግ ነው ሚኒስትር ዴኤታው የጠቆሙት።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2017 የብሔራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ትግበራ በተጀመረበት ወቅት በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚዎች ተደራሽነት 44 በመቶ ነበር።
በአሁኑ ሰዓት በሀገር አቀፍ ደረጃ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚዎች 52 በመቶ መድረሱን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ቀሪውን የሕብረተሰብ ክፍል የኤሌክትሪክ አቅርቦት እንዲያገኝ የማድረግ ሥራ የጋራ ርብርብ እንደሚጠይቅ አመልክተዋል።
በተያያዘም ከተለያዩ የኢነርጂ ምንጮች የኤሌክትሪክ ኃይልና የብርሃን ተደራሽነት ማስፋት ዓላማ ያደረገው “አዴል” ለተሰኘው ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የዓለም ባንክ 500 ሚሊየን ዶላር መልቀቁንና ፕሮግራሙን ወደ ትግበራ ማስገባት የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን ገልፀዋል።
መርሃ-ግብሩ የብሔራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራምን ትግበራ ከመደገፍ አኳያ የራሱ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያብራሩት።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ አሁን ያላትን ኢኮኖሚ መሸከም የሚችል የኢነርጂ ኃይልና ለቀጣናው የኤሌክትሪክ ኃይል ሥራ መንግሥት ብቻውን የሚሸፍነው አይደለም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ከዚህ አኳያ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
መንግሥት የግሉ ዘርፍ የኢነርጂ ልማት ተሳትፎን ለማሳደግ የመንግሥትና የግል አጋርነት የሕግ ማዕቀፍን ጨምሮ የተለያዩ አሠራሮች ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
የኢነርጂ ዘርፍ አቅምና ፍላጎቶች የተመለከቱ መረጃዎች ለግሉ ዘርፍ እየቀረቡ መሆኑንና የዘርፉ ተዋንያን በኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ሥራው ተሳትፎ እያደረጉ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የታዳሽ ኃይል ኩባንያ አሚያ ግሩፕ በሶማሌ ክልል ሽንሌ ሲቲ ዞን አይሻ ወረዳ የ300 ሜጋ ዋት የነፋስ ኃይል ፕሮጀክት ግንባታ እያከናወነ እንደሚገኝ ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት።
በኦሮሚያ ክልል ቱሉሞዬ እና በሲዳማ ክልል ኮርቤቲ የእንፋሎት ኃይል ፕሮጀክቶች ግንባታ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ማሳያ ናቸው ብለዋል።
የአረብ ሀገራት፣ እስያና አውሮፓ ሀገራት በኢነርጂው ዘርፍ ለመሰማራት ያላቸው ፍላጎት ማሳየታቸውንና በኢትዮጵያ በዘርፉ እምቅ ዕድሎችና አማራጮች እንዳሉ ለመረዳት መቻላቸውን አመልክተዋል።