በኢትዮጵያ ለዘመናዊ አስተዳደርና ለሳይንሳዊ ግኝቶች ብዘሃ ባህሎችና አገር በቀል ዕውቀቶች ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ተገለጸ

175

ጂንካ፤ ሚያዚያ 8/2016(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ለዘመናዊው የአስተዳደር ስርአትም ሆነ ለሳይንሳዊ ግኝቶች በብዝሃ ባህሎች ውስጥ ያሉ ሀገር በቀል እውቀቶች ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው አንድ የዘርፉ ተመራማሪ ገለጹ።

በባህልና በታሪክ ላይ ያተኮረ ሀገር አቀፍ አውደ ጥናት በጂንካ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል።


 

በአውደ ጥናቱ ላይ የተሳተፉት የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል አንትሮፖሎጂ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ዶናልድ ኤል ዶነሃም እንደገለጹት ኢትዮጵያ አስደናቂ ባህሎችና ሀገር በቀል ዕውቀት አሏት።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ከ50 ዓመታት በላይ የጥናትና ምርምር ስራዎችን እንዳካሄዱ የገለጹት ተመራማሪው፣ በማህበረሰብ ጥናት በፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ላይ ያጠነጠኑ የተለያዩ መጻህፍትን ለህትመት እንዳበቁም ተናግረዋል።

በአፍሪካ በጥናትና ምርምር ከቆዩባቸው ዓመታት በኢትዮጵያ የቆዩበት ጊዜ እንደሚበልጥ ገልጸው፣ ኢትዮጵያ በድንቅ መልክአ ምድሮች እና ብዝሃ ባህሎች የታደለች ሀገር መሆኗን አንስተዋል።

ፕሮፌሰሩ በአውደ ጥናቱ ላይ "የኢትዮጵያ አመሰራረት እና የሀገር በቀል እውቀቶች ለግጭት አፈታት" በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።

ተመራማሪው ባቀረቡት ጽሁፍ በኢትዮጵያ አሁን ላለው ዘመናዊ አስተዳደርና ለሳይንሳዊ ግኝቶች ከብዝሃ ባህሎች የተቀዱ ሀገር በቀል ዕውቀቶች ትልቅ ድርሻ እንዳላቸውም አመላክተዋል።

በኢትዮጵያ አብሮነትን ለማጠናከርና ሰላምን ለማፅናት በሀገር በቀል ዕውቀቶች ውስጥ የሚገኙ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑንም አንስተዋል።

እነዚህ እሴቶች ለዘመናዊው አስተዳደርና ለሳይንሳዊ ግኝቶች ያላቸውን አቅም ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት በጥናትና ምርምር አጎልብተው ማውጣትና ጥቅም ላይ እንዲውሉ መስራት አለባቸው ብለዋል።

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ፣ የምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ኤሊያስ አለሙ፤ አውደ ጥናቱ የታሪክ ተመራማሪዎችንና የማህበረሰብ አጥኚዎችን በአንድ በማሰባሰብ ልምድና ዕውቀቶችን ለመለዋወጥ የታሰበ መሆኑን ገልፀዋል።


 

ይህም በቀጣይ በጥናትና ምርምር ሥራዎች ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት ጋር በትብብር ለመስራት ያስችላል ነው ያሉት።

እንደ ሀገር ባህላዊ ሀብቶች ለማህበረሰባዊ የኑሮ ዘይቤ የሚኖራቸውን አስተዋጽኦ በጥናት በማስደገፍ ጥቅም ላይ እንዲውሉና እንዲሸጋገሩ ከማድረግ አንጻር የሚያነቃቃ መሆኑንም ተናግረዋል።

የዩኒቨርሲቲው የሶሻል አንትሮፖሎጂ መምህርና ተመራማሪ መምህሩ ገዙሜ በበኩላቸው እንደሀገር ከፖለቲካዊ አስተዳደር ባሻገር ለአጠቃላይ ማህበረሰብ የሚጠቅሙ የባህል ሀብቶች እንዳሉ ተናግረዋል።


 

እነዚህ ሀብቶች በአግባቡ ተሰንደውና በምርምር ተደግፈው ጥቅም ላይ ከመዋል አንጻር ያለውን ክፍተት ለመሙላት ብዘሃ ባህሎች ላይ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በስፋት ማካሄድ እንደሚገባ ግንዛቤ ያገኙበት መሆኑንም ገልጸዋል።

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲን በመወከል በአውደ ጥናቱ ላይ የተሳተፉት የሶሻል አንትሮፖሎጂ መምህርትና ተመራማሪ ዶክተር ሀና ጌታቸው፤ አውደ ጥናቱ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ያገኘንበት ነው ብለዋል።


 

የማህበረሰብ አጥኚዎች በአንድ አካባቢ ብቻ መታጠር እንደሌለባቸው አንስተው፣ የዘርፉ ተመራማሪዎች የሌሎች ባህሎችን መዳሰስ እንዲሁም የተዘነጉና የተደበቁ በርካታ ጠቃሚ እሴት ያላቸው ባህሎችን ለማውጣት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

በአውደ ጥናቱ ላይ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተጋበዙ ጥናት አቅራቢዎች፣ የዘርፉ ምሁራንና የማህበረሰብ ተወካዮች ታድመዋል።

 


 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም