የአድዋ ድል መታሰቢያን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከ31ሺህ በላይ ሰዎች ጎብኝተውታል

164

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 8/2016(ኢዜአ)፡- የአድዋ ድል መታሰቢያን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከ31ሺህ በላይ ሰዎች መጎብኘታቸውን የድል መታሰቢያው ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ውባየሁ ማሞ ገለጹ።

የአድዋ ድል መታሰቢያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም በይፋ የተመረቀ ሲሆን ለሕዝብ ዕይታ ክፍት ተደርጎ በመጎብኘት ላይ ይገኛል።


 

በአምስት ሄክታር ላይ ያረፈው የድል መታሰቢያው በአንድነት የተከፈለውን መስዋዕትነት በሚያሳይ መልኩ በኪነ-ሕንጻ ጥበብ የታነጸ ነው።

የአድዋ ድል መታሰቢያ መግቢያ በሮችም የምሥራቅ ጀግኖች በር፣ የምዕራብ ጀግኖች በር፣ የሰሜን ጀግኖች በር፣ የደቡብ ጀግኖች በር፣ የፈረሰኞች በር፣ የአርበኞች በር፣ የፓን አፍሪካኒዝም በር ተብለው ተሰይመዋል።

ከሀገርም በመሻገር የአፍሪካውያን ብሎም የመላ ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ምልክት የሆነው የአድዋ ድል መታሰቢያ መጋቢት 7 ቀን 2016 ዓ.ም ለሕዝብ እይታ ክፍት ሆኖ በየእለቱ በርካቶች እየጎበኙት መሆኑ ተገልጿል።

የአድዋ ድል መታሰቢያ ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ውባየሁ ማሞ፤ የድል መታሰቢያው ለህዝብ ክፍት ከተደረገ ጀምሮ በየእለቱ በርካታ ጎብኚዎችን እያስተናገደ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ከመጋቢት 7 እስከ ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ባለው የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ 31 ሺህ 750 ሰዎች እንደጎበኙትም ተናግረዋል።

የድል መታሰቢያውን የተቋማት ሰራተኞች፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ተማሪዎችም ጭምር እየጎበኙት ስለ አድዋ ታሪክም ጥሩ ግንዛቤ እያገኙ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በአዲስ አበባ በየካቲት ወር 2016 ዓ.ም በተካሄደው 37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የተሳተፉ የሀገራት መሪዎች፣ ዲፕሎማቶችና ልዑካን የአድዋ ድል መታሰቢያን መጎብኘታቸው ይታወቃል።

ከህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ በተጓዳኝም ኢትዮጵያ ያዘጋጀቻቸው ሁነቶች በዚሁ የድል መታሰቢያ መካሄዳቸው ይታወሳል።

ከ2ሺህ 500 በላይ እንግዶችን መያዝ የሚችል ፓን አፍሪካን አዳራሽ፣ 300 ሰዎች የሚይዝ የአድዋ አዳራሽ፣ 160 ሰዎች የሚይዝ መካከለኛ አዳራሽ፣ 300 ሰው በአንድ የሚያስተናግዱ ሬስቶራንቶች፣ ሁለት ካፍቴሪያዎችና የህጻናት ሙዚየምን በውስጡ አካቷል።

በአንድ ጊዜ 1000 ተሽከርካሪ መያዝ የሚችሉ ፓርኪንግ፣ ዘመናዊ ጂምና ሌሎች መሰረተ ልማቶችንም የያዘ መሆኑ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም