ቀጥታ፡

የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት እየተባባሰና ጥፋትም እያስከተለ ነው- የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 8/2016(ኢዜአ)፡-  የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት እየተባባሰና ጥፋትም እያስከተለ መሆኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት ያለበትን ሁኔታ የተመለከተ የዳሰሳ ጥናት ሪፖርት ይፋ አድርጓል።


 

የሪፖርቱ ዓላማ የማኅበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች በአዋጁ መሠረት ግዴታቸውን በምን ያህል መጠን እየተወጡ መሆናቸውን ማመላከት መሆኑ ተገልጿል።

የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት የሚገኝበትን ሁኔታ እና እያስከተለ ያለውን ተጽዕኖ በሚመለከትም መፍትሔ ተመላክቷል።

በዚሁ መሠረት ሪፖርቱ መረጃዎቹ በሁለት መንገድ መሰባሰቡ ተገልጿል።

የመጀመሪያው ከፌስቡክ፣ ቲክቶክ፣ ቴሌግራም፣ ዩ-ቲዩብ እና ኤክስ በናሙና መረጃዎች መሰብሰባቸው ተገልጿል።

ሁለተኛው የሕዝብ አስተያየት ማካተት በማስፈለጉ በአምስት ክልሎች በመጠይቆች እና በነፃ የስልክ መስመር መረጃዎች መሰብሰባቸው ታውቋል።

በተሰበሰበው መረጃ መሠረትም የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት እየተባባሰና ጥፋትም እያስከተለ መሆኑ ተመላክቷል።

የባለሥልጣኑ የመገናኛ ብዙኃን አቅም ግንባታ ዴስክ ኃላፊ ኤደን አማረ በሰጡት ማብራሪያ፤ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ እየተስፋፋ መሆኑን ከመረጃው መረዳት ችለናል ብለዋል። 

የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ መስፋፋቱ ደግሞ በተለይም በግለሰቦችና አጠቃላይ በኅብረተሰብ ደኅንነት ላይ አደጋ ደቅኗል ነው ያሉት።

ከጥላቻ ንግግር ምንጮች መካከልም በዋነኝነት አንዳንድ የሃይማኖት አባቶች፣ አክቲቪስቶች፣ ፖለቲከኞች፣ የማኅበራዊ ይዘት አመንጪዎችና ግለሰቦች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በስድስት ወራት በተደረገው የዳሰሳ ጥናት መሠረት የጭካኔ አገላለጽ የሚስተዋልበት የመረጃ ሥርጭት በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረበትና በተለይም በቴሌግራም 65 በመቶ የሥርጭት ድርሻ እንዳለው አንስተዋል።

የጥላቻ ንግግሮቹ  በብሔር፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋ እና ሌሎች የወል ማንነቶች ላይ በስፋት ያነጣጠረ መሆኑም ተመላክቷል ነው ያሉት።

በግለሰቦች፣ በቡድኖች፣ በተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ ፖለቲከኞችና በባለሥልጣናት ላይም እንዲሁ።

የሐሰት አውድ እና የተሳሳተ መረጃ እንዲሁም በፈጠራ የተቀነባበረ ይዘት ያለው መረጃዎች በብዛት የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ የሚሰራጭባቸው መንገዶች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

በጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት ቀደም ሲል የብሔር ተኮር ማንነቶች ላይ በስፋት ያነጣጠረ እንደነበር አስታውሰው፤ ከቅርብ ወራት ወዲህ ደግሞ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ አተኩሯል ብለዋል።

በተለያዩ ቅንብሮች የጭካኔ ድርጊቶችን በማጉላት የዜጎች ስጋትና ጥርጣሬ እንዲያይል የማድረግ ሁኔታዎችም በስፋት መንፀባረቃቸውን ጠቁመዋል።

በመሆኑም የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት ከፍተኛ ችግር እየሆነ በመምጣቱ የመከላከልና መግታት ጉዳይ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም ነው ያሉት።

በተለይም የማኅበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ሰጪዎች ባወጡት አሠራር መሠረት ደንብና መመሪያዎችን አክብረው ግዴታና ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም