ቀጥታ፡

በክልሉ በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች ፈጥነው ወደ ማምረት እንዲገቡ ተጠየቀ

አሶሳ፤ ሚያዝያ 08/2016 (ኢዜአ)፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች ፈጥነው ወደ ማምረት በመግባት ኢኮኖሚውን እንዲደግፉ ተጠየቀ፡፡

አምስተኛው የክልሉ ግብርና ኢንቨስትመንት ፎረም ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተጀምሯል፡፡


 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መሬት እና የህብረት ስራ ማደራጃ ቢሮ ሃላፊ አቶ ቢኒያም መንገሻ በፎረሙ መክፈቻ ላይ እንዳሉት  ክልሉ ካለው እምቅ ሃብት መካከል ለግብርና ኢንቨስትመንት የሚሆን ለም መሬት አንዱ እና ዋነኛው ነው፡፡

በክልሉ የተሻለ የመሬት አስተዳደር አጠቃቀም ስርዓት እንዲኖር በማድረግ ህብረተሰቡ ብሎም መንግስት ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆን ሰፊ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ሃላፊው አክለዋል፡፡

በክልሉ ባለፉት ዓመታት አንድ ሺህ 312 በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች 532 ሺህ 293 ሄክታር መሬት ቢረከቡም በተግባር ወደ ስራ የገቡት ግን ውስን መሆናቸውን ቢሮው ማረጋገጡን አቶ ቢኒያም አመልክተዋል፡፡

አሁን በክልሉ የመጣውን ሠላምና ምቹ የአገልግሎት አሰጣጡን በመጠቀም ለግብርና ኢንቨስትመንት የወሰዱትን መሬት ሙሉ በሙሉ በማልማት ፈጥነው ወደ ማምረት መግባት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

ቢሮው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ለባለሃብቶቹ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግም አቶ ቢኒያም አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌደራል ተቋማትም የሚጠበቅባቸውን በማድረግ የክልሉ ግብርና ኢንቨስትመንት እንዲነቃቃ ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የእርሻ እና ሆልቲካልቸር ኢንቨስትመንት አስተባባሪ አቶ  አማኑኤል ገብረስላሴ በፎረሙ ተገኝተው የሀገሪቱን የግብርና ኢንቨስትመንት የተመለከተ ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡

በጽሁፋቸው የኢትዮጵያ ግብርና ኢንቨስትመንት አቅምን አሟጦ ማምረት ከተቻለ ዘርፉ ድህነትን ለማስወገድ የሚያስችል በርካታ ምቹ አጋጣሚዎች እንዳሉት አብራርተዋል፡፡

ሀገሪቱ ለአውሮፓ እና ለመካከለኛው ምስራቅ ሀገሮች ቅርብ እና ስትራቴጂክ ቦታ ላይ መገኘቷን ገልጸው ይህም የግብርና ምርት ያለውን ሰፊ የገበያ አማራጭ እንደሚያሳይ አስተባባሪው ጠቅሰዋል፡፡

የግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲጠናከር በመንግስት በኩል ከፍተኛ ድጋፍ መደረጉን ጠቁመው፤ መሬት ማስተላለፍ ከፌደራል ወደ ክልሎች ሃላፊነት መሰጠቱና ለባለሃብቶች የተለያዩ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች እና ሌሎችም ድጋፎች ያካተተ አዋጅ መጽደቁን በአብነት ጠቁመዋል፡፡

በመድረኩ በክልሉ የሚገኙ በግብርናው ዘርፍ ባለሃብቶች፣ የዘርፉ ባለሙያዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም