ኢትዮ-ቴሌኮም አካታች የዲጂታል ስርዓትን ለማረጋገጥ የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ ይቀጥላል- ፍሬህይወት ታምሩ 

291

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 8/2016(ኢዜአ)፡-  ኢትዮ-ቴሌኮም ዲጂታል ፋይናንስን ጨምሮ በሁሉም መስክ አካታች የዲጂታል ስርዓት ለማረጋገጥ የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮ- ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገለጹ።

ኢትዮቴሌኮም  "ቴሌ ብር-ኢንጌጅ" የተሰኘ አዲስ መተግበሪያ ትናንት ምሽት ይፋ አድርጓል።

በአገልግሎቱ ደንበኞች የቢዝነስ የተናጥል ወይም የቡድን ቀጥታ ውይይቶችን ለማድረግ፣ የግብይት መረጃዎችን ለመለዋወጥ፣ ገንዘብ ለመላክና ለመቀበል እንደሚያስችል ገልጸዋል። 

እንዲሁም የቢዝነስ ወይም ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮቻቸውን በፅሁፍ፣ በፎቶ፣ በድምጽ፣ በቪዲዮና በሰነድ መልክ መለዋወጥ ይችላሉ ነው ያሉት።

በመረሃ ግብሩ- ላይ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ  ፍሬህይወት ታምሩ እንደገለጹት፣ኩባንያው ዲጂታል ኢትዮጵያን በሁሉም ዘርፍ  እውን ለማድረግ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው።


 

በተለይ የዲጂታል ፋይናንስ ስርዓቱን ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ "ቴሌ ብር- ኢንጌጅ" መተግበሪያ በዲጂታል ፋይናንስ ሽግግር ውስጥ የንግድ፣ የመንግስትና የግል ተቋማትን ትኩረት በማድረግ የዲጂታል ኢኮኖሚ ምህዳሩን ለማስፋፋት የሚረዳ  ነው ብለዋል።

ኩባንያው በአገር አቀፍ ደረጃ የገነባቸው መሰረተ ልማቶች ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎችን በማገዝ ረገድ ሚናቸው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ኩባንያው አዳዲስ የዲጂታል አገልግሎቶችን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም የዲጂታል ፋይናንስ አካታችነትን ለማሳደግ ከ3 ዓመት በፊት ይፋ ባደረገው ቴሌ ብር አማካኝነት በየቀኑ  የ5 ቢሊዮን ብር ግብይት የሚከናወን ሲሆን፤  በ3 ዓመታት ውስጥ 2 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ብር የገንዘብ ዝውውር ተደርጎበታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም