የሸዋል ኢድ በዓልን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ የባህል ዐውደ ርዕይና ፌስቲቫል በሐረር ከተማ ተከፈተ

ሐረር፤ ሚያዚያ 8/2016(ኢዜአ)፡-የሸዋል ኢድ በዓልን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ የባህል ዐውደ ርዕይና ፌስቲቫል በሐረር ከተማ  ዛሬ ተከፈተ።

የባህል ዐውደ ርዕዩንና ፌስቲቫሉ የተከፈተው የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ፣የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ እና የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ  በተገኙበት ነው።


 

በባህል ዐውደ ርዕዩና ፌስቲቫሉ አጎራባች ክልሎች እና የአርጎባ የባህል ቡድን እንዲሁም የባህል አልባሳትና ጌጣጌጥ አምራች ማህበራትና ተቋማት ተሳትፈዋል።

እንዲሁም ሚኒስትሮችና ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ አምባሳደሮች፣ የፌዴራልና የክልሉ የሥራ ሃላፊዎች፣ አባ ገዳዎችና ሌሎች እንግዶች በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተዋል።

የሸዋል ኢድን አስመልክቶ የተዘጋጀው የባህል ዐውደ ርዕዩና ፌስቲቫሉ  የብሔር ብሔረሰቦችን ግንኙነት እንደሚያጠናክር የሐረሪ ክልል የባህል፣ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ ሃላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ ተናግረዋል።


 

እንዲሁም አንዱ ክልል የሌላውን ባህልና ትውፊት እንዲረዳና ወንድማማችነትን ለማጎልበት እንዲያግዝ መሆኑን አመልክተዋል።

"ሸዋል ኢድ ለህብረ ብሔራዊ አንድነታችንና ለቱሪዝም እድገታችን" በሚል መሪ ሐሳብ የተዘጋጀው የባህል ዐውደ ርዕይና ፌስቲቫል ለሁለት ቀናት እንደሚቆይ አቶ ተወለዳ ተናግረዋል።


 

በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም በማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገቡን የሚገልጽና ከዩኒስኮ የተሰጠ የሸዋል ኢድ የምስክር ወረቀት ቢል ቦርድ በክብር እንግዶቹ በከተማው ተመርቋል።

የሸዋል - ኢድ በዓል የኢድ አልፈጥር በዓል ከተከበረበት ቀን ጀምሮ ለተከታታይ ስድስት ቀናት ከተፆመ በኋላ ከስድተኛው ቀን ምሽት ጀምሮ እስከ ማግስቱ 10 ሰዓት ድረስ የሚከበር ነው።


 

በዓሉ  በሐረሪ ብሔረሰብ ወጣቶች ትኩረት የሚሰጠው እና በታዳሚው ዘንድ አብሮነትን እና ወንድማማችነትን እያጎለበተ የመጣ በዓል ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም