ዴንማርክ ለኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ልማት የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች

71

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8/2016(ኢዜአ)፡- ዴንማርክ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን የግብርና ዘርፍ ልማት ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች፡፡

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) በዴንማርክ የልማት ፖሊሲ ምክር ቤት ሊቀ-መንበር አን ሜት ኪጀር ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡


 

ኢትዮጵያና ዴንማርክ በዘርፈ-ብዙ ጉዳዮች በተለይም በግብርናው ልማት ዘርፍ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸው በውይይቱ ተነስቷል፡፡

ዴንማርክ በግብርናው ዘርፍ ለኢትዮጵያ እያደረገች ያለው ድጋፍና አጋርነት በቀጣይም ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ ምክክር አድርገዋል፡፡

ግብርና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዋነኛው ዘርፍ መሆኑንና ወደ ተሻለ ምርታማነት ለማሸጋገር በሚደረገው ርብርብም ዴንማርክ እስካሁን ላደረገችው ድጋፍ የግብርና ሚንስትሩ ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) አመስግነዋል፡፡

ግብርናውን ለማዘመን ሰፊ ስራዎች ስለመከናወናቸውና የአየር ንብረት ለውጥ በግብርናው ዘርፍ ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ለመቀነስ ላለፉት 5 አመታት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በመተግበር 32.78 ቢሊዮን ችግኝ መተከሉን ሚንስትሩ ለልዑካን ቡድኑ ገልጸዋል፡፡

በመስኖ ስንዴ ልማትና በሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቮች እየተመዘገበ ያለው ውጤት የግብርናውን ዘርፍ በእጅጉ እያሳደገው ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡

መንግስት በግብርናው ዘርፍ በተለይም በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም፣ በግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ክላስተር፣ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል የአረንጓዴ ልማትና በሌሎችም ስራዎች እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ለልዑካን ቡድኑ ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡

የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት በማሳደግ የዘርፉንና የምግብ ስርዓት ሽግግር እውን ለማድረግ መንግስት የሚያከናውነውን ተግባር ለመደገፍ ዴንማርክ እያደረገች ያለውን ድጋፍ በቀጣይም አጠናክራ እንድትቀጥል በውይይቱ ወቅት ተነስቷል፡፡


 

የልዑካን ቡድኑም በግብርናው ዘርፍ በተለይም በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም፣ በግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ክላስተርና በአረንጓዴ ልማት እየተሰሩ ባሉ ስራዎች ላይ ስለተደረገላቸው ገለፃ ማመስገናቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም