ስንዴን በተለያዩ አማራጮች በማልማት ከውጭ የሚገባውን ምርት ማስቀረት ተችሏል - ግብርና ሚኒስቴር

104

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 8/2016(ኢዜአ)፡- መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትልቅ ትኩረት ስንዴን በተለያዩ አማራጮች በማልማት ከውጭ የሚገባውን ምርት ማስቀረት መቻሉን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን(ዶ/ር) ገለጹ። 
 
ሚኒስትር ዴኤታው በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ያለውን የስንዴ ልማት ተሞክሮ ለመቅሰም ከመጡ የናይጄሪያዋ ጅጋዋ ከተማ ልኡክ ጋር ውይይት አድርገዋል።


 

በውይይቱም ስንዴን መሰረት ያደረገ የሃብት ብልጽግና ለመፍጠር የመስኖ ስንዴ እርሻ ማስፋፊያ፣ የግብዓት አቅርቦትና የብድር አገልግሎት በስፋት ማቅረብ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።

ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን ኢትዮጵያ ስንዴን በጥራት እና በብዛት እያመረተች መሆኑን  ለልኡካኑ ገልጸው በዚህም በስንዴ ምርት ራሷን ከመቻል አልፋ ለውጭ ገበያ እያቀረበች ትገኛለች ብለዋል።

መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትልቅ ትኩረት  ስንዴን በተለያዩ አማራጮች በማልማት ከውጭ የሚገባውን ምርት ማስቀረት እንደተቻለም አብራርተዋል።


 

ከናይጄሪያዋ ጅጋዋ ከተማ የመጡ ልኡካን በበኩላቸው በስንዴ ምርት እራስን ከመቻል አልፎ ምርትን ለውጪ ገበያ በማቅረብ ኢትዮጵያ የማይቻለውን የቻለች ሀገር ናት ብለዋል።

ልኡካኑ ይህን ምርጥ ተሞክሮ ወደ ሀገራቸው ለማስፋፋት በሚሰሩ ስራዎች የኢትዮጵያን እገዛ እንደሚፈልጉም ገልጸዋል።

ከሳህራ በታች ከሚገኙ ሀገራት ትልቋ የስንዴ አምራች ሀገር ኢትዮጵያ የስንዴ ቴክኖሎጂ እንዲስፋፋ የሚያግዝ የምርምር ማዕከላት ያቋቋመች ሲሆን የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችሉ 145 የስንዴ ዝርያዎችን ማስተዋወቅ እንደተቻለ የግብርና ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።

በኢትዮጵያ የናይጀሪያ አምባሳደር አሚኑ ናጊር ከልኡካን ቡድኑ ጋር በመሆን በውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም