ኢትዮጵያ ለስታርት አፖች ከፋይናንስ አቅርቦት ጀምሮ ምቹ ምህዳርን የሚፈጥሩ የፖሊሲ እርምጃዎችን መውሰድ ጀምራለች-ዶክተር ብሩክ ታዬ

559

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 7/2016(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ለስታርት አፖች ከፋይናንስ አቅርቦት ጀምሮ ምቹ ምህዳርን የሚፈጥሩና ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር የሚተገበሩ ጠንካራ የፖሊሲ እርምጃዎችን መውሰድ መጀመሯን የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ገለጹ።

በኢትዮጵያ የሚገኙ ስታርት አፖች ፈንድ ሊያገኙ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በሳይንስ ሙዚየም ተካሂዷል።

ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት መንግስት ስታርት አፖች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በተቀናጀ መልኩ ለመቅረፍ እየሰራ ነው።


 

ኢትዮጵያ ለስታርት አፕ ምቹ ምህዳርን ለመፍጠር ከፋይናንስ አቅርቦት፣ ከህግ፣ ከመሰረተ ልማትና ሌሎች ጉዳዮች አኳያ ጠንካራ የፖሊሲ እርምጃዎች መውሰድ መጀመሯን ለልማት አጋሮች አብራርተዋል።

ይህንን ለማጠናከርም መንግስት ከልማት አጋሮች፣ ከግሉ ዘርፍና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ለስታርት አፖች ውጤታማነት ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን አንስተው፥ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ውይይቶችም እየተካሄዱ ስለመሆኑ  አስረድተዋል።


 

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም የአካታች እድገት እና ዘላቂ ልማት የኢትዮጵያ ቡድን መሪ የሆኑት ግዛቸው ሲሳይ በበኩላቸው፥ ስታርት አፖች በፋይናንስ እጥረት ምክንያት የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት ከመንግስት ጋር በትብብር እየሰራን ነው ብለዋል። 

የመንግስታቱ የልማት ፕሮግራም ከብሔራዊ ባንክ እና ከኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ጋር በመሆን የፈጠራ ፋይናንስ አሰራርን መዘርጋቱን ተናግረዋል።

በዚህም የቴክኒክ ድጋፍ እና ብድር ለስታርት አፖች እንዲቀርብ ይደረጋል ነው ያሉት።


 

የዓለም ባንክ ተወካይ ማርሎን ረውሊንስ እንዳሉት ባንኩ በኢትዮጵያ ለተለያዩ የልማት እና የድህነት ቅነሳ ፕሮግራሞች ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

ሀገሪቱ የጀመረችው የዕድገት ጉዞ እንዲሳካ በቀጣይ  ድጋፉን እንደሚቀጥል ጠቅሰው በተለይ በኢትዮጵያ በጅምር ላይ ያለው የስታርት አፕ ምቹ ምህዳርን ለማስፋት የቴክኒክ ድጋፎችን ያደርጋል ብለዋል።

ባንኩ የስራ ዕድል ፈጠራን ለማበረታትም ስታርት አፖችን የማማከር፣  ፕሮጀክታቸው ላይ ግብረ መልስ በመስጠት የማገዝ ስራን ጨምሮ ሁሉን አቀፍ የድጋፍ ዕይታን  እንደሚከተል ጠቁመዋል።

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም