በክልሉ በሚገኙ የባለበጀት መስሪያ ቤቶች የዘጠኝ ወራት የፋይናንስ አስተዳደር የሚፈትሽ ድጋፋዊ ግምገማ ዛሬ ተጀምሯል

203

ሀዋሳ ፤ ሚያዚያ 7/2016(ኢዜአ)፡-  በሲዳማ ክልል በሚገኙ የባለበጀት መስሪያ ቤቶች የዘጠኝ ወራት የፋይናንስ አስተዳደር የሚፈትሽ ድጋፋዊ ግምገማ ዛሬ መጀመሩን የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ የፋይናንስ ቢሮው ሃላፊ ዶክተር አራርሶ ገረመው በዚሁ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

የድጋፋዊ ግምገማ ዓላማውም በክልሉ ከመንግስትና ከተለያዩ አማራጮች የሚመጣ ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ማስቻል መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ በጅት ያለምንም ብክነት የህዝብ የልማት ጥያቄ ሊመልስ በሚችል መልኩ እንዲውል ቢሮው ጠንካራ የሆነ የቁጥጥርና የምዘና ስርዓት ዘርግቶ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በክልሉ 106 ባለበጀት መስሪያ ቤቶች መኖራቸውን የጠቀሱት ሃላፊው፤ እያንዳንዱ መስሪያ ቤት የሚመደብለትን ገንዘብ ለህዝብ ፍላጎት የማዋል ግብ ስለማሳካቱ ቁጥጥርና ክትትል ይደረጋል ብለዋል።

የንብረትና ገንዘብ አያያዝና አስተዳደር፣ ሪፖርት ማድረግና አያያዝ፣ የግዥ ስርዓትን ጨምሮ ከዘርፉ ጋር ተያያዥነት ባላቸውና የአገር ዓቀፉንና ዓለም አቀፉን የፋይናንስ አሰራር በተከተሉ 26 የመገምገሚያ መስፈርቶች እንደሚፈተሹም አንስተዋል።

በበጀት ዓመቱ ከተበጀተው ከ22 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር 34 በመቶ ለካፒታል ፕሮጀክቶች የተመደበ መሆኑን አስታውሰዋል።

በአጠቃላይ በክልሉ የህዝብ ፍላጎት መሰረት በልዩ ትኩረት እየተከናወኑ የሚገኙ የውሃ፣ የመንገድ፣ የጤናና ሌሎች መሰረተ ልማቶች በጀቱ እየዋለ ስለመሆኑ በአግባቡ እንደሚፈተሽ ተናግረዋል።

የክልሉን የፋይናንስ ስርዓት ግልጽ እና ቀልጣፋ ለማድረግ የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓት ለመዘርጋት የዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በክልሉ ባለፉት የዘጠኝ ወራት የፋይናንስ ስርዓት ለመፈተሽ የተጀመረው ድጋፋዊ ግምገማ ለሁለት ሳምንታት የሚቆይ ሲሆን፤ የተሻለ አፈጻጸም ያሳዩትን ማበረታታትና ጉድለት የሚታይባቸውን ማረም ዓላማ ያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም