በዓለም ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የመንግስታትና የሃይማኖት ተቋማት የትብብር ስራ ወሳኝ ነው - ዶክተር ከይረዲን ተዘራ

438

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 7/2016(ኢዜአ)፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የመንግስታትና የሃይማኖት ተቋማት ቅንጅታዊ ስራ ወሳኝ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ከይረዲን ተዘራ ገለጹ።

የ37 የዓለም ሀገራት የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች የተሳተፉበት ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ተቋማት የምክክር ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

በጉባዔው የሃይማኖት መሪዎች፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ አምባሳደሮች፣ የአፍሪካ እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ከይረዲን ተዘራ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት በሃይማኖት መቻቻልና መከባበር የምትታወቅ ሀገር ናት፡፡


 

ሁሉም ሃይማኖቶች በጎነትንና ሰላምን በመስበክ ለሀገርና ለትውልድ በአብሮነት መቀጠል ጉልህ አሻራ ማሳረፋቸውንም ገልጸዋል።

መንግስት የሃይማኖት ተቋማት በሰላም ግንባታና በሀገራዊ አንድነት ላይ ቁልፍ ሚና እንዳላቸው በፅኑ በማመን በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በቅርቡ ከተለያዩ የእምነት አባቶች ጋር በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያደረጉትን ውይይት በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የመንግስታትና የሃይማኖት ተቋማት ቅንጅታዊ ስራ ወሳኝ መሆኑንም ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያመላከቱት፡፡

ኢትዮጵያ የጋራ እሴቶችን ይበልጥ በማጠናከር ከራሷ ባለፈ በአፍሪካና በተቀረው የዓለም ክፍል ለሰው ልጆች ሰላምና ደህንነት በትብብር መስራቷን አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሓን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው፤ የሃይማኖት ተቋማት ዋና ፍላጎትና ስራቸው በምድሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ነው ብለዋል፡፡



ይህ እውን እንዲሆንም የዓለም መንግስታትና ህዝቦች መነጋገር፣ መደማመጥ፣ ልዩነቶች እንኳ ቢኖሩ በንግግር መፍታት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

ሠላምና ልማትን ማረጋገጥ፣ ሰብዓዊ ክብርንና አካባቢን መጠበቅ፣ የጥላቻ ንግግርንና መጤ ጠልነትን በጋራ ለመከላከል አበክሮ መስራት እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ የቡድን 20 የሃይማኖት ትስስር ማህበር ፕሬዘዳንት ፕሮፌሰር ኮል ዱርሐም ናቸው፡፡



ላምን ማህበረሰባዊ እሴትነት ለማጎልበትም የሃይማኖት ተቋማት ሃላፊነት እንዳለባቸው ጠቅሰዋል።

የምክክር መድረኩ የሃይማኖት ተቋማቱ በጋራ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ አቋም በመያዝ ወደ ተግባር እንዲገቡ ለማድረግ ሚናው ከፍተኛ ነውም ብለዋል፡፡

"የሃይማኖት ተቋማት ትብብር ሰላምን፣ ሰብዓዊ ክብርን፣ ልማትን፣ አካባቢ ጥበቃን፣ ማጠናከርና የጥላቻ ንግግርን ግጭትንና ጠባብ ብሔርተኝነትን መቃወም" በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሔደ ያለው የምክክር መድረክ ነገም የሚቀጥል ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም