በበጀት ዓመቱ 9 ወራት ከአስር ቢሊዮን ብር በላይ የመንገድ ፈንድ ገቢ ተሰበሰበ

214

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 7/2016(ኢዜአ)፡- በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ለመንገዶች ጥገና እና የመንገድ ደህንነት ማስፈጸሚያ የሚሆን ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ የመንገድ ፈንድ ገቢ መሰብሰቡን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ።

በተሰበሰበው ገቢ የወቅታዊና መደበኛ የመንገድ ጥገና ሥራዎች መከናወናቸውም ነው አስተዳደሩ የገለጸው።

ገቢው የተገኘው በነዳጅ ላይ ከተጣለ ታሪፍ፣ ከተሽከርካሪ ዘይትና ቅባት፣ ከመንገድ ጠቀሜታ ክፍያ እና በክብደት ላይ የተመሰረተ ዓመታዊ የተሽከርካሪ ፈቃድ ማደሻ መሆኑም ተመልክቷል።

የተሰበሰበውን ገቢ ለመንገድ ጥገና ከማዋል አንፃር በዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ ባቀረቡት የክፍያ ሰርቲፊኬት መሰረት የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር(ኢመአ) 4 ቢሊዮን 163 ሚሊዮን 410 ሺህ 907 ብር ከ23 ሳንቲም፣ የክልል ገጠር መንገድ ኤጀንሲዎች 1 ቢሊዮን 726 ሚሊዮን 478 ሺህ 976 ብር ከ99 ሳንቲም መከፈሉን ከአስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

በተጨማሪም የከተማ መንገድ ኤጀንሲዎች 916 ሚሊዮን 865 ሺህ 104 ብር ከ27 ሳንቲም እንዲሁም ለድጋፍ ሰጪ(የአማካሪ ክፍያ) 17 ሚሊዮን 471 ሺህ 811 ብር ከ59 ሳንቲም፣ ለመንገድ ደህንነት እና መድን ፈንድ አገልግሎት 26 ሚሊዮን 519ሺህ 109 ብር ከ14 ሳንቲም እና የባንክ፤ ለፖስታ ቤት ኮሚሽን ክፍያ 12ሚሊዮን 770 ሺህ 80 ብር ከ33 ሳንቲም በአጠቃላይ በመንገድ ጥገና ጥቅም ላይ እንዲያውሉ 6 ቢሊዮን 863 ሚሊዮን 515 ሺህ 989 ብር ከ55 ሳንቲም መከፈሉን ገልጿል፡፡

የተመደበው በጀት ለተገቢው አገልግሎት መዋሉን ከማረጋገጥ አኳያ በአስተዳደሩ፣ በክልል እና በከተማ የመንገድ ኤጀንሲዎች በሚያስተዳድሯቸው ፕሮጀክቶች ላይ የመስክ ቅኝት የማድረግና የምህንድስና(ቴክኒካል) ኦዲት ሥራ መከናወኑም በመረጃው ተገልጿል።

አስተዳደሩ በበጀት ዓመቱ 9 ወራት ከመንገድ ፈንድ የሰበሰበው ገቢ 10 ቢሊዮን 356ሚሊዮን 19ሺህ 307 ብር ከ40 ሳንቲም መሆኑንም አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም