በኮንሶ ዞን አንድ ሺህ አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የሶላር ሃይል ፕሮጀክት 70 በመቶ ተጠናቋል -- ሚኒስቴሩ

219

ካራት ፤ ሚያዚያ 7/2016(ኢዜአ)፡-  በኮንሶ ዞን አንድ ሺህ አባወራዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በ100 ሚሊዮን ብር  ወጪ እየተገነባ ያለው የሶላር ሃይል ፕሮጀክት 70 በመቶ መጠናቀቁን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ የሚመራ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልና የኮንሶ ዞን ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ፕሮጀክቱን ዛሬ ጎብኝተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው በዚህ ወቅት እንዳሉት እንደ አውሮፓውን አቆጣጠር በ2030 የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከሚያገኘው የኢትዮጵያ ሕዝብ 35 በመቶውን በሶላር ሃይል ለመሸፈን እየተሠራ ነው።

መስሪያ ቤቱ የኤሌክትሪክ ሀይል የማያገኙ የገጠር ነዋሪዎችን የሶላር ሃይል ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች 650 ኪሎ ዋት ሃይል ማመንጨት የሚችሉ አምስት የሶላር ሃይል ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እየተከናወኑ ካሉ የሶላር ሃይል ፕሮጀክቶች በኮንሶ ዞን ኬና ወረዳ ጌራ ቀበሌ በ100 ሚሊዮን ብር  ወጪ እየተገነባ ያለው ፕሮጀክት አንዱ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት የግንባታ ስራው የተጀመረው ፕሮጀክት በአሁኑ ወቅት 70 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ በመጪው ሰኔ ወር ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃም ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ አንድ ሺህ አባወራዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ዶክተር ኢንጂነር ሱልጣን ገልጸዋል።

በሀገር ደረጃ ባለፉት 10 ዓመታት ዋናው ሃይል የማይደርስባቸው አካባቢዎች ላይ ሀይል ለማዳረስ በተከናወኑ ስራዎች 320 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ የሶላር ሃይል በሁሉም ክልሎች በመገንባት ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ፕሮጀክቶቹ ኅብረተሰቡን የሃይል ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ለመስኖ ልማት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳላቸው ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።

የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገልጌሎ ገልሾ በዞኑ ከፍተኛ የሃይል ተደራሽነት ችግር መኖሩን ጠቅሰው፣ ፕሮጀክቱ ከመሠረተ ልማት ርቆ ለሚኖር ሕዝብ መገንባቱ ፋይዳውን የላቀ  ያደርገዋል ብለዋል።


 

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ኅብረተሰቡን የሃይል ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ የእህል ወፍጮ፣ የእንጨትና ብረታ ብረት ሥራዎችን መስራት ስለሚያስችል ለወጣቱ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።

የሕዝቡን የዘመናት የመልካም አስተዳደር ችግር ለሚፈታው ለዚህ ፕሮጀክት ተገቢው ጥበቃ ማድረግ እንደሚገባም አስተዳዳሪው ተናግረዋል።

ማህበረሰቡ ማገዶ እንጨት የሚጠቀም በመሆኑ በደን ሀብት ላይ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በኮንሶ ዞን ኬና ወረዳ ጌራ ቀበሌ ነዋሪ አቶ በላቸው ቦራንቶ ናቸው።


 

ለብዙ ዓመታት በአካባቢያችን የኤሌክትሪክ ሃይል ባለመኖሩ ጨለማ ውስጥ ኖረናል ያሉት ነዋሪው፣ ፕሮጀክቱ ሥራ ሲጀምር በተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚያሳድረውን ጫና ከማስቀረት ባለፈ የዘመናት የሀይል ችግራችንን ይፈታል ብለዋል። 

በኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት 300 የሶላር ሃይል ፕሮጀክቶችን በመገንባት ለሕዝብ የሃይል ስርጭቱን በፍትሀዊነት ለማዳረስ እየተሠራ መሆኑን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም