የኦሮሞ ባህልና ኪነ-ጥበብ የህዝቡን አንድነት የሚያስጠብቅ ሆኖ እንዲቀጥል ትኩረት ተደርጓል

170

አዲስ አበባ ሚያዚያ 07/2016(ኢዜአ)፦የኦሮሞ ህዝብ ባህልና የኪነ-ጥበብ ውጤቶች የህዝቡን አንድነት የሚያስጠብቁ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር አብዱልዓዚዝ ዳውድ ገለጹ።

የኦሮሞ ህዝብ ባህላዊ ትውፊቶች የሚታዩበት ኤግዚቢሽን በኦሮሞ ባህል ማዕከል የተከፈተ ሲሆን በተለያዩ የኪነ-ጥብብ ዘርፎች ለሦስት ወራት የሰለጠኑ ወጣቶችም ተመርቀዋል።
 
በመርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ መንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ አባ ገዳና ሃዳ ሲንቄዎች፣ የኪነ-ጥባብ ባለሙያዎችን ጨምሮ የተለያዩ እንግዶች ታድመዋል።


 

ኃላፊው በዚህ ጊዜ እንዳሉት የክልሉ ባህልና ኪነ-ጥበብ ተጽዕኖ የሚፈጥርና የህዝቡን አንድነት የሚያስጠብቅ እንዲሆን የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

ባህልና ኪነ-ጥበብ የአንድ ህዝብ ትልቅ መገለጫ ነው ያሉት ዶክተር አብዱልአዚዝ ትውልዱ በዘርፉ በቂ እውቅት እንዲኖረው የተጀመረው የግንዛቤ ማስጨበጥና የማስተዋወቅ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስረድተዋል።

ባህልና ኪነ-ጥበብ በዘመን ሂደት የህዝብን አንድነትና ባህል ከማጠናከርና ከማስተዋወቅ አንጻር ትልቅ አስተዋጽኦ ያላቸው መሆኑንም አንስተዋል።
 
የኦሮሚያ ክልል መንግስትም የኦሮሞ ህዝብ ባህልና ኪነ-ጥበብ ውጤቶች የህዝቡን አንድነት የሚያስጠብቁ እንዲሆኑ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጿል።
 
በተለይም የቀደመው ትውልድ የራሱን ተሰጥኦ ተከትሎ በጎ አሻራዎችን ማሳረፉን አስታውሰው የአሁኑ ትውልድ ደግሞ በባህልና ኪነ-ጥበብ ዙሪያ ዘመኑን የሚመስል እውቀት መጨበጥ አለበት ብለዋል።
 
''ኪነ ጥበብ ከዘመን ጋር እንዲራመድ ለማስቻል የቀደመው ትውልድ በሰራው ስራ ላይ መሻሻሎች እንዲኖሩ ወጣቱን ትውልድ እውቀት የማስጨበጡ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል'' ነው ያሉት።




  
የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ጀሚላ ሲምቢሮ በበኩላቸው፣ የባህልና ኪነ ጥበብ ዘርፉ ከህዝብ መገለጫነት በላፈ በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት ብለዋል።
 
ባህልና ኪነ-ጥበብ የህዝቡን አንድነት፣ ህብረትና ትብብር ከማጠናከር በተጨማሪ ለወጣቶች እንደ ስራ እድል መፍጠሪያ ጥቅም ላይ ሊውል ይገባል ብለዋል።
 
ወጣቶች የህዝቡን ባህልና ኪነ-ጥብብ ለማሳደግና ለማስተዋወቅ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ተጨማሪ እወቅት እየጨበጡ ህዝባቸውን የበለጠ እንዲጠቅሙ የሚያደርግ መሆኑንም አክለዋል።



  
የኦሮሞ ባህልና ኪነ-ጥበብ የህዝቡን አንድነት ማስጠበቅ፣ ህዝቡን ማነቃቃት፣ የአገር ፍቅር ያለው ህብረተሰብ ለመገንባትና ሰላምን ለማጽናት ትልቅ አስተዋ ማበርከቱን የገለጹት ደግሞ የኦሮሞ ባህል ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ መኪያ ጀማል ናቸው።
 
ባህልና ኪነ-ጥበብ የበለጠ ለህዝቡ የጋራ ጥቅም እንዲውል ወጣቶችን እውቀት የማስጨበጡ ስራ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች እንደሚከናወን ገልጸዋል። 
 
በተለያዩ የኪነ-ጥበብ ዘርፎች ለሦስት ወራት የሰለጡ ወጣቶች በበኩላቸው በአገኙት እውቀት የህዝቡን በህልና ማንነት ለማስተዋወቅ እንደሚተጉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም