ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት በመከላከል ሂደት የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ የሚያሳድግ የአሰራር ማዕቀፍ ተዘጋጀ

154

አዳማ፤ ሚያዚያ 7/2016(ኢዜአ)፡-  ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት በመከላከል ሂደት የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ የሚያሳድግ  የአሰራር ማዕቀፍ መዘጋጀቱን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

ዛሬ በአዳማ ከተማ ከፍትህና ጤና ሚኒስቴር እንዲሁም የክልሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የብሔራዊ የስርዓተ ጾታ ጥቃት መከላከልና ምላሽ መስጠት የአሰራር ማዕቀፍ የማስጀመሪያ መድረክ ተካሄዷል፡፡

በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዲኤታ ማእረግ የሚኒስትሯ አማካሪ  አቶ ጌታቸው በዳኔ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት የአሰራር ማዕቀፉ በተለይም ቀድሞ የነበረውን የአሰራር ወጥነት ችግር ለመቅረፍ ያግዛል፡፡


 

የአሰራር ማዕቀፉ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሰውን ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት ለመከላከልና ተጋላጭነትን ለመቀነስ እንዲሁም ጥራቱን የጠበቀ የምላሽ ስራዎችን ለማከናወን ሁሉም ባለድርሻ አካላት መከተል ያለባቸውን የአሰራር ስርዓት የያዘ መሆኑን ገልጸዋል። 

በዋናነትም ቀድሞ ይታዩ የነበሩ የአሰራር ወጥነት ችግሮችን በመቅረፍ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችና ህፃናት የተሟላ አገልግሎት እንዲያገኙ የተቋቋመውን የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተደራሽነቱን ለማረጋገጥም ትልቅ እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

ማዕቀፉ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጾታዊ ጥቃት መከላከል ሂደት ተጋላጭነትን መቀነስ የሚያስችሉ አሰራሮችን ተግባራዊ እንዲያደርጉም አቅጣጫ የሚያመላክት ነው ብለዋል።

ማዕቀፉ አላማውን እንዲያሳካ የጋራ ትብብራቸው አስፈላጊ የሆኑት ፍትህ፣ ጤና ሚኒስቴር፣ ፖሊስና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት መረባረብ እንደሚገባቸውም አመላክተዋል፡፡

በጉዳዩ ቀጥተኛ ኃላፊነት ከተጣለባቸው ባለድርሻ አካላት መካከልም የፍትህ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ኤርሚያስ የማነብርሃን፣ ፆታዊ ጥቃትን ለመመከት የሚያግዝ ወጥ የአሰራር ማዕቀፍ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ማዕቀፉ ከሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ክፍተቶችን አስወግዶ ውጤታማ ስራዎችን ለመስራት የተዘጋጀ በመሆኑ በዚህ ረገድ ግዴታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።


 

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬህይወት አበበ በበኩላቸው ማዕቀፉ በጾታዊ ጥቃት ምክንያት እየደረሰ ያለውን የጤናና ተያያዥ ችግሮች ለመከላከል የሚረዳ መሆኑን አክለዋል።

በጤና ሚኒስቴር ዘርፍ በአሰራር ማዕቀፉ መሰረት የሚፈጸሙ ተግባራትን በማዘጋጀት እስከ ክልሎች በማውረድ የማስተባበር ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም