ቀጥታ፡

የሸዋል ኢድ በዓልን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ጎብኝዎች ለማስተዋወቅ አራት ሙዚየሞች ተመርጠው ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው- የኢትየጵያ ቅርስ ባለስልጣን

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 7/2016(ኢዜአ)፡- የሸዋል ኢድ በዓልን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ጎብኝዎች  በዘላቂነት ለማስተዋወቅ አራት ሙዚየሞች ተመርጠው  የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን አስታወቀ።

የሸዋል ኢድ በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የትምህርት ተቋም (ዩኔስኮ) በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት ህዳር/2016 ዓ.ም መመዝገቡ ይታወቃል።

በዓሉ በዩኔስኮ ከተመዘገበ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነገ በተለያዩ ስርዓቶች በሀረር ከተማ በድምቀት ይከበራል።

የሸዋል ኢድ በዓልን ለማስተዋወቅ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን  አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ኤሊያስ ሽኩር፤ የሸዋል ኢድ በዓልን በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ ደረጃ የማስተዋወቅ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

በተለይም በዓሉ ባህላዊ ይዘቶቹን ጠብቆ እንዲጎለብትና ለአካባቢውን ተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን ወደ ስራ መገባቱንም ጠቁመዋል።

ለዚህም ከሐረሪ ክልል አስተዳደርና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ጥንታዊቷ የሐረር ከተማ የበርካታ ቅርሶች መገኛ በመሆኗ በርካታ ቱሪስቶች ለጉብኝት ወደ ስፍራው እንደሚያቀኑ ጠቅሰዋል።


 

በመሆኑም የሸዋል ኢድና ሌሎች ቅርሶች በአግባቡ ተጠብቀው እንዲጎለብቱና ለቱሪዝም ዘርፉ ያላቸው አበርክቶ እንዲያድግ ትኩረት መሰጠቱን አንስተዋል።

የሸዋል ኢድ በዓልን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ጉብኝዎች በይበልጥ ለማስተዋወቅም በሐረር ከተማ አራት ሙዚየሞች  ተመርጠው የተለያዩ ዝግጅቶችና የቅርስ ልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዓሉ በሐረሪ ክልል ሕዝባዊ እና ባህላዊ በዓል ሆኖ እንዲከበር ጥቅምት 8/1999 ዓ.ም በአዋጅ በመደንገጉ በሐረሪ በድምቀት የሚከበር በዓል ነው።

ሸዋል ኢድ የሚከበርባት ሐረር የጥንታዊት ኢትዮጵያ የሥልጣኔ ማሳያ ተብላ  የምትጠቀስ ሲሆን በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በወቅቱ ሐረርን ያስተዳድሯት የነበሩት አሚር ኑር፣ ከተማዋን ከጥቃት ለመከላከል የገነቡት የጁጎል ግንብ በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል።

ይህ ቅርስ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም እ.ኤ.አ በ2006 የተመዘገበ ሲሆን አምስት በሮች አሉት።

በ7ኛው ክፍለ ዘመን የተቆረቆረችው ጥንታዊቷ ሐረር፥ በዓለም ቅርስነት  የተመዘገቡትን የጁጎል ግንብ እና የሸዋል ኢድ በዓልን ጨምሮ የበርካታ የመስህብ ስፍራዎች መገኛ ናት። 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም