ከውጭ የሚገቡ የማምረቻ መሳሪያዎችን በሀገር ውስጥ መተካት የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ ነው - አቶ መላኩ አለበል - ኢዜአ አማርኛ
ከውጭ የሚገቡ የማምረቻ መሳሪያዎችን በሀገር ውስጥ መተካት የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ ነው - አቶ መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 7/2016(ኢዜአ)፡- የማሽነሪ አምራቾች ከውጭ የሚገቡ የማምረቻ መሳሪያዎችን በሀገር ውስጥ መተካት የሚያስችል አቅም እየፈጠሩ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።
በአሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድ የኢንዱስትሪ ምርት ወጪ ንግድን በማሳደግ 9 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር የሚደርስ ገቢ ለማስገኘት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ትብብር ሀገር አቀፍ የማሽነሪ አምራች ኢንዱስትሪ ዕድልና ተግዳሮት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፤ የኢንዱስትሪ ዕድገትን ለማሳለጥ የተኪ ምርት፣ የቆዳና ኬሚካል ልማት፣ የማሽነሪና የትስስር ስትራቴጂክ ዕቅዶች ተቀርጸው ስራ ላይ መዋላቸውን ገልጸዋል።
በ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድም ወጪ ንግድን በማሳደግ 9 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር የሚደርስ ገቢ ከዘርፉ ለማግኘት ግብ መያዙን ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም 5 ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር እንዲሁም የሀገር ውስጥ ምርት የገበያ ድርሻን ከ30 በመቶ ወደ 60 በመቶ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
አዳዲስ ኢንተርፕራይዞችን በማልማትም ከ50 በመቶ በታች የነበረውን የማምረት አቅም ወደ 85 በመቶ ለማሳደግም በ10 ዓመቱ ዕቅድ ትኩረት መደረጉን አስረድተዋል።
የዘርፉን የልማት ግብ ለማሳካት አምራቾች በመስሪያ ቦታ፣ በማምረቻ መሳሪያ፣ በገበያ ትስስር፣ በፋይናንስና ግብዓት አቅርቦት ላይ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ ነው ብለዋል።
በማሽነሪ ምርትና መለዋወጫ ምርታማነትን በማሳደግ ከውጭ የሚገቡ የማሽነሪ ጥሬ እቃ አቅርቦትና ፍላጎቶችን በራስ አቅም ማጣጣም እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ የጥራት ደረጃና የስራ ተስማሚነትን በሟላ ሁኔታ የተመረቱ አንዳንድ የማሽነሪ ምርቶችንም ወደ ውጭ መላክ እንደተጀመረ ተናግረዋል።
በማሽነሪ አምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ እየተፈጠረ ያለው አቅም ከውጭ የሚገቡ የማምረቻ መሳሪያዎችን በሂደት በሀገር ውስጥ ለመተካት ምቹ ምኅዳር እየፈጠረ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር አለባቸው ንጉሴ (ዶ/ር)፤ ባለፉት አምስት ዓመታት ከ15 ሺህ በላይ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራዞች መፈጠራቸውን አንስተዋል።
በአዲስ መልክ ወደስራ ለገቡ ኢንተርፕራይዞችም የፋይናንስ ብድርና የማሸነሪ ሊዝ ፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል።
ለማሽነሪ አምራቾች በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እየተደረገ የሚገኘው ድጋፍም የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች መፍታት የሚያስችል ምቹ ምኅዳር እየተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
ማሽነሪ አምራቾችም ራሳቸውን በማደራጀት ምርትና አገልግሎታቸውን በማስተዋወቅ የገበያ ትስስር ችግሮችን እየፈቱ ነው ብለዋል።
የፌደራልና የክልል የስራ ኃላፊዎች፣ የማሽነሪ አምራችና አቅራቢዎች በተገኙበት በዛሬው መድረክ መንግስት የኢንዱስትሪ ሽግግርን በማሳለጥ ሀገራዊ የጥቅል ምርት ድርሻው 17 በመቶ እንዲደርስ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።
መንግስት የሀገር ውስጥ አምራቾችን ለማበረታታት "በኢትዮጵያ ታምርት፤ ኢትዮጵያ ትሸምት" መርሃ ግብር ውጤታማ የገበያ ትስስር እየተፈጠረ መምጣቱም ተመላክቷል።
በመድረኩ የማሽነሪ አምራች ኢንዱስትሪዎች ዕድሎችና ተግዳሮቶች እንዲሁም ቀጣይ ስራዎችን የሚያመላክቱት ጽሁፎች ቀርበው ጥያቄ፣ አስተያየት፣ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።